በጀልባ መገልበጥ አደጋ የ16 ኢትዮጵያውያን ህይወት አለፈ፤ 28 መንገደኞች ጠፍተዋል
77 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከየመን የባህር ዳርቻ አሳፍራ ወደ ጅቡቲ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ጎዶሪያ በሚባል አካባቢ ተገልብጣለች
በጀልባዋ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ 33ቱ በህይወት መትረፋቸው ተገልጿል
የጀልባ መገልበጥ አደጋ የ16 ኢትዮጵያውያንን ህይወት ቀጠፈ።
ትላንት ምሽት ከየመን የባህር ዳርቻ ልዩ ስሙ አራ ከሚባል ስፍራ 77 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሳፍራ ወደ ጅቡቲ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ጎዶሪያ በሚባል አካባቢ መገልበጧን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
በዚህም እስካሁን ድረስ አምስት ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ 16 ሰዎች ህይወት ማለፉን ነው ኤምባሲው የገለጸው።
በጀልባዋ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ 28ቱ እስካሁን አልተገኙም ያለው መግለጫው፥ 33 ፍልስተኞች ተርፈው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አመላክቷል።
አለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በሁለት ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ በደረሰው አደጋ ህጻናትና ሴቶችም ተጎጂ ሆነዋል ሲል በኤክስ ገጹ አስፍሯል።
በጂቡቲ የሚገኘው የተቋሙ ቢሮም በነፍስ አድን ስራው ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ነው የጠቆመው።
ከሁለት ሳምንት በፊትም ከጂቡቲ የባህር ጠረፍ 200 ሜትር ርቀት ላይ በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ የ38 ኢትዮጵያውያን ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው።
ከጅቡቲ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚደረገው ህገወጥ ጉዞ በየጊዜው የዜጎቻችንን ህይወት እያሳጣን ይገኛል ያለው በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፥ ዜጎች በዚህ አደገኛ የጉዞ መስመር ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
የፍትህ አካላትም ከገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍሎች ዜጎችን በመመልመል ለስደት በሚዳርጉ ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።
የአለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት እንደሚለው በየአመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው ከኢትዮጵያ የሆኑ የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች በየመን በኩል ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለመግባት ይሞክራሉ።
በየመን ያለው ሁኔታ ጉዟቸውን ሲያሰናክለውም ጊዜ ለመግዛት ወደ ጅቡቲ እንደሚመለሱ ነው የሚገልጸው።