የብሪታንያ ፓርላማ አከራካሪውን ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅድ አጸደቀ
ስደተኞችን የጫኑ አውሮፕላኖች ከ10 እስከ 12 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ኪጋሊ መብረር ይጀምራሉ ተብሏል
በህገወጥ መንገድ ብሪታንያ የገቡና የጥገኝነት ጥያቄያቸው ምላሽ ያላገኘ 52 ሺህ ሰዎች ወደ ሩዋንዳ እንደሚላኩ ይጠበቃል
የብሪታንያ ፓርላማ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅድ አጸደቀ።
ከሁለት አመት በላይ ውዝግብ ሲነሳበት የቆየውና ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሽ ሱናክ ይፋ ያደረጉት እቅድ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ በሩዋንዳ እንዲቆዩ የሚያደርግ ነው።
በብሪታንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ህገወጥ” ነው ተብሎ ውድቅ የተደረገው፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች “ከሰብአዊነት የራቀ ነው” በሚል ሲተቹት የቆዩት እቅድ ትናንት በብሪታንያ ፓርላማ ህግ ሆኖ እንዲወጣ ድምጽ ተሰጥቶበታል።
ይህን ተከትሎም ከ10 እስከ 12 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በአውሮፕላኖች ወደ ሩዋንዳ ማጓጓዝ እንደሚጀመር ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚዎቻቸው ህጉ እንዳይፈጸም ግፊታቸውን እንዲቀጥሉ ያደርጋል በሚል ምን ያህል ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ስለመታቀዱ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ቢቢሲ ግን በህገወጥ መንገድ ወደ ብሪታንያ የገቡ ከ52 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ኪጋሊ እንደሚላኩ ነው የዘገበው።
ይሁን እንጂ ወደ ሩዋንዳ እንዲመለሱ የሚወሰንባቸው ስደተኞች በፍርድቤት ይግባኝ መጠየቅና መከራከር ይችላሉ መባሉ የእቅዱን በተያዘለት ጊዜ ተፈጻሚነት ጥርጣሬ ውስጥ ከቶታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በበኩላቸው የየትኛውም ሀገር ፍርድ ቤት ህጉን ተፈጻሚ ከማድረግ አያግደንም ሲሉ ተደምጠዋል።
በ2022 በአነስተኛ ጀልባዎች 45 ሺህ 774 ህገወጥ ስደተኞች ወደ ብሪታንያ የገቡ ሲሆን፥ ባለፈው አመት አሃዙ ወደ 29 ሺህ 437 ዝቅ ብሏል።
ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላኩ እቅድ ተፈጻሚ ከሆነም ወደ ብሪታንያ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር በእጅጉ መቀነስ ይቻላል ተብሏል።
ብሪታንያ ወደ ሩዋንዳ ለምትልካቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች በነፍስ ወከፍ 215 ሺህ ዶላር እንደምታወጣ ማሳወቋ የሚታወስ ነው።