በናይጀሪያ 160 ሰዎች በታጣቂዎች ታግተው ተወሰዱ
በሀገሪቱ ኒጀር ግዛት በተፈጸመ ጥቃት 10 ሰዎች መገደላቸውም ተገልጿል
የቦኮ ሀራም ታጣቂዎች ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ንጹሃንን በማገት የማስለቀቂያ ገንዘብ እንደሚጠይቁ ይታወቃል
በናይጀሪያ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 10 ሰዎች መገደላቸውና ቢያንስ 160 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ተነገረ።
በማዕከላዊ ኒጀር ግዛት ኩቺ በተባለች መንደር የተፈጸመውን ጥቃት እና እገታ የቦኮሃራም ታጣቂዎች ሳይፈጽሙት እንዳልቀሩ ተገምቷል።
በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች መንደሯን በሞተር ሳይክሎች እንደከበቧት የሚያወሱት የአካባቢው አስተዳዳሪ አሚኑ አቡዱልሃሚድ ናጁሜ፥ በመንደሯ ምግብ ሰርተው በመብላት፣ ሻይ በማፍላትና ቤቶችን እየተዘዋወሩ በመዝረፍ ለሁለት ስአታት ቆይታ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
አብዛኞቹ የተገደሉትና ታግተው ወዳልታወቀ ቦታ የተወሰዱት ሰዎችም ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን በመጥቀስ።
የኩቺ መንደር ከዚህ ቀደምም መሰል ጥቃትና እገታ የተደጋገመባት መሆኗን በማስታወስም ከትናንት በስቲያ የታገቱ ንጹሃን ደህንነት አሳሳቢ ነው ብለዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ 160 ሰዎች በታጣቂዎች መታገታቸው “የናይጀሪያ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት ማስጠበቅ እንደተሳነው ማሳያ ነው” ብሏል።
የኩቺ መንደር ከ2021 ጀምሮ የታጠቁ ሃይሎች የሚዘርፏትና ነዋሪዎቿን የሚያግቱባት መሆኗን በመጥቀስም ንጹሃን ከእገታ ለማምለጥ ለታጣቂዎች በሚሊየን የሚቆጠር ናይራ (የናይጀሪያ ገንዘብ) መክፈል እንደሚጠበቅባቸው አስታውሷል።
በናይጀሪያ ቦኮሃራምን ጨምሮ የታጠቁ ሃይሎች ንጹሃንን በማገት የማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቅ ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል።
የሀገሪቱ መንግስት በተለያየ ጊዜ የታገቱ ሰዎችን እንዳስለቀቀ ቢገልጽም አሁንም ድረስ እገታው አልቆመም።
በታጣቂዎች ታግተው የሚወሰዱ ሴቶች እየተደፈሩም በልጅነታቸው የልጅ እናት እየሆኑ ነው የሚሉ ዘገባዎች ሲወጡ ቆይተዋል።