ናይጀሪያውያን አሳሳቢ ችግር ገጥሞታል ላሉት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ፀለዩ
ካኖ በተባለው ግዛት የሚኖሩ ነጋዴዎች “ፈጣሪ ጣልቃገብቶ የኑሮ ምስቅልቅሉን እንዲፈታው” የአንድነት ጸሎት አድርገዋል
የናይጀሪያ መንግስት የነዳጅ ድጎማን ካነሳ በኋላ የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ ነው ተብሏል
ናይጀሪያውያን አሳሳቢ ችግር ገጥሞታል ላሉት የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ፀለዩ።
የጨርቃጨርቅ ምርት በስፋት በሚመረትባት ካኖ ግዛት የሚኖሩ ነጋዴዎች ናቸው በጋራ ተሰብስበው ጸሎት ያደረጉት።
ሱቃቸውን ዘግተው ለጋራ ጸሎቱ የተሰባሰቡት ነጋዴዎ “ፈጣሪ ጣልቃገብቶ የኑሮ ምስቅልቅሉን ይፍታው እንጂ የናይጀሪያ መንግስት ባለስልጣናትንስ ጉዳይ ሆድ ይፍጀው” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ሃሚሱ ሳኒ የተባለ አንድ ነጋዴ የኑሮ ውድነቱ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ መሆኑንና በርካቶች በልተው ለማደር መቸገራቸውን ተናግሯል።
“ይህን ልዩ ጸሎት በጋራ የምናደርገው ፈጣሪ እንዲረዳን ነው፤ ምክንያቱም የሀገራችን መንግስት ንረቱን ለማስቆም ምን እያደረገ እንደሚገኝ የምናውቀው ነገር የለም” ሲልም ነው ብሶቱን የገለጸው።
በናይጀሪያ በአሁኑ ወቅት ሩዝ እና ስኳር የቅንጦት ሸቀጦች መሆናቸውን በመጥቀስም “ከዚህ ምስቅልቅል ለመውጣት የምንተማመነው በፈጣሪ እርዳታ ብቻ ነው” ብሏል።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ከፍተኛ ነው የተባለ የዋጋ ግሽበት አጋጥሟል።
የታህሳስ ወር 2023 የዋጋ ግሽበትም 28 ነጥብ 9 በመቶ መሆኑን የሀገሪቱ ብሄራዊ ስታስቲክስ ቢሮ መረጃ ያሳያል።
ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ በግንቦት ወር 2023 ስልጣን እንደያዙ የነዳጅ ድጎማ መነሳቱን ይፋ ማድረጋቸውም የዋጋ ግሽበቱን እንዳባባሰው ነው የተነገረው።
ለነዳጅ ድጎማ በየወሩ 500 ሚሊየን ዶላር ታወጣ የነበረችው ናይጀሪያ፥ ድጎማው ጥቂት ኩባንያዎችን ብቻ መጥቀሙን በመጥቀስ ለተለያዩ መሰረተልማቶች ማሟያ ባደርገው ይሻላል ብላለች።
ፕሬዝዳንት ቲኑቡ ከ220 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ሀገራቸው የገጠማትን አሳሳቢ የኑሮ ውድነት ለማቃለል ቃል መግባታቸውም የሚታወስ ነው።