የናይጀሪያ መንግስት “በስህተት” በፈጸመው የድሮን ጥቃት 85 ሰዎች ተገደሉ
ካዱና በተባለችው ግዛት ታጣቂዎችን ለመምታት የተላከች ድሮን ሃይማኖታዊ በዓል ሲያከብሩ የነበሩ ሰዎችን መታለች ተብሏል
በናይጀሪያ ጦር በንጹሃን ላይ የቦምብ ጥቃት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው አይደለም
የናይጀሪያ መንግስት ጦር በታጣቂዎች ላይ ለመፈጸም ያቀደው የድሮን ጥቃት በስህተት በጥቂቱ የ85 ንጹሃንን ህይወት መቅጠፉ ተነግሯል።
ካዱና በተባለችው ግዛት ሃይማኖታዊ በዓል ለማክበር የተሰባሰቡ ሙስሊሞች ላይ በስህተት ተፈጽሟል የተባለው ጥቃት በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውም ነው የተገለጸው።
የግዛቷ አስተዳዳሪ “አሸባሪዎች እና ሽፍቶችን” ኢላማ ያደረገው የድሮን ጥቃት በስህተት ንጹሃንን ገድሏል ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በዚህ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 120 እንደሚደርስ በናይጀሪያ የሚገኘው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ቢሮ አስታውቋል።
በርካታ ሰዎች በጽኑ በመቁሰላቸውም የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ነው የተነገረው።
የአካባቢው ነዋሪዎች ሌላ “በስህተት የሚፈጸም ጥቃትን” ፍራቻ መፈናቀላቸውም ተገልጿል።
የናይጀሪያ መንግስት “በስህተት” ንጹሃን ላይ የቦምብ ጥቃት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በየካቲት 2014 የሀገሪቱ ጦር አውሮፕላን በቦርኖ ግዛት ዳግሉን በተባለ አካባቢ የቦምብ ጥቃት ፈጽሞ ከ20 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል።
በመስከረም 2022 ብቻ ከ14 በላይ ኢላማቸውን የሳቱ ከ14 በላይ የቦምብ ድብደባዎች የበርካታ ንጹሃንን ህይወት መቅጠፉንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የናይጀሪያ ጦር በሰሜን ምዕራብ እና ማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ታጣቂዎች እና ሽፍታዎች መደበቂያዎች ላይ እርምጃ ሲወስድ ነው በስህተት የንጹሃን መኖሪያዎች ኢላማ የሚሆኑት።
ይሁን እንጂ በስህተት ተፈጸሙ ለተባሉት ጥቃቶች አንድም ሰው ተጠያቂ አለመሆኑና በተደጋጋሚ የመከሰቱ ጉዳይ በመብት ተሟጋቾች ተቃውሞ እያስተናገደ ነው።