አይስላንድ ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ 17 ሺ ገደማ ርዕደ መሬት ማስተናገዷ ተነገረ
“ምድር ለአንድ ሳምንት ሙሉ 24 ሰዓት ስትንቀረቀብ ማየት ለተፈጥሮ ትንሽና አቅም አልባ እንደሆንክ እንዲሰማህ የሚያደርግ ነው”- የሬይካቪክ ነዋሪ
ከባድ ነበር የተባለለት መንቀጥቀጥ ሳምንት ረቡዕ ጠዋት ያጋጠመ ነው ተብሏል
ምንም እንኳን ለተደጋጋሚ ርዕደ መሬቶች እና እሳተ ገሞራ አዲስ ባትሆንም አይስላንድ ባሳለፍነው ሳምንት ግን ለየት ያሉ ሁኔታዎች ገጥመዋት ነበር ተባለ፡፡
ሬይካንስ የተባለው ደቡብ ምዕራባዊ የሃገሪቱ አካባቢ ባለፈው ሳምንት ብቻ 17 ሺ ገደማ ርዕደ መሬቶችን ማስተናገዱን የሃገሪቱ ሜቲዮሮሎጂ ቢሮ ያስታወቀው፡፡
ከባድ ነበር የተባለው መንቀጥቀጥ ሳምንት ረቡዕ ጠዋት ያጋጠመ ነው፡፡ መንቀጥቀጡ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 6 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
መንቀጥቀጡ ሃገሪቱ ዋና ከተማ ሬይካቪክ ድረስ የተሰማ ከፍተኛ ንዝረት ነበረው የተባለ ሲሆን ነዋሪዎች ለከፍተኛ መደናገጥ ተዳርገው ነበርም ተብሏል፡፡
ሬይካቪክ ከደሴቲቷ ሃገር አጠቃላይ ህዝብ ሁለት ሶስተኛ ያህሉ የሚኖርበት ከተማ ነው፡፡
በሬክተር ስኬል ከ5 በላይ ሆነው የተመዘገቡ ሁለት መንቀጥቀጦች ባሳለፍነው ቅዳሜ እና ሰኞ አጋጥመውም ነበር ብሏል ሜቲዮሮሎጂ ቢሮው፡፡
በርዕደ መሬቱ የደረሰ የጎላ ሰብዓዊ ጉዳት የለም፡፡ ሆኖም በአንዳንድ መንገድን መሰል መሰረተ ልማቶች ላይ የመንቃት (መሰንጠቅ) እና የናዳ ሁኔታዎች እንደነበሩ ነው የተገለጸው፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ አጋጥሞኛል በእንዲህ ያለ ሁኔታ ግን ሆኖ አያውቅም ሲሉ አስተያየታቸውን ለሲኤንኤን የሠጡ አንድ የከተማው ነዋሪ ምድር ለአንድ ሳምንት ሙሉ 24 ሰዓት ስትንቀረቀብ ማየት ለተፈጥሮ ትንሽ እና አቅም አልባ እንደሆንክ እንዲሰማህ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
350 ሺ ገደማ ህዝብ ያላት አይስላንድ ለእንዲህ ዓይነት ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች እንደሚጋለጥ በሚነገርለት የምድር አካባቢ መገኘቷን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡