እ.ኤ.አ በ2015 በፓሪስ የተፈረመውን ስምምነት 200 የዓለማችን ሃገራት ፈርመዋል
አሜሪካ የፓሪሱን የአየር ንብረት ስምምነት ዳግም መቀላቀሏል አስታወቀች፡፡
ዋሽንግተን ወደ ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ስምምነት የተመለሰችው በአዲሱ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ውሳኔ ነው፡፡
ባይደን ዳግም ወደ ስምምነቱ እንደሚመለሱ ወደ ነጩ ቤተመንግስት በገቡ ዕለት ነበር ያስታወቁት፡፡
ይህን ባሉ በአንድ ወር ውስጥም ተግብረውታል፡፡ ይህም ፕሬዝዳንቱን አስመስግኗቸዋል፡፡ የአየር ንብረት ተመራማሪ ሳይንቲስቶች እና የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ሳይቀሩ ውሳኔውን አድንቀዋል፡፡
ባይደን በቀጣዮቹ 3 አስርታት የካርቦን ልቀትን በእጅጉ የመቀነስ ውጥን አላቸው፡፡
ይህን የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ የአየር ንብረት መልዕክተኛቸው [የቀድሞው የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር] ጆን ኬሪ በበይነ መረብ በሚካሄድ እና የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ የእንግሊዝ እና የጣሊያን አምባሳደሮች በሚገኙበት መርሃ ግብር በይፋ ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነበሩ አሜሪካ በ2015 በፈረንሳይ ፓሪስ በ200 የዓለማችን ሃገራት ከተፈረመው ስምምነት ራሷን እንድታገል ያደረጉት፡፡
ምክንያታቸው ስምምነቱ የአሜሪካን ብሄራዊ ጥቅም የሚጎዳ ነው የሚል ነበር፡፡