በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ግዛት ሄሊኮፕተር ተከስክሶ የሁሉም ተሳፋሪዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ
ባለፈው ቅዳሜ ከግንኙነት ራዳር ውጭ ሆና የነበረችው ሄሊክፕተር 19 ጎብኝዎችን እና ሶስት ሰራተኞችን ይዛ ነበር
ሄሊኮፕተሯ በተከሰከሰችበት ካምቻትካ የደረሱት የነፍስ አድን ሰራተኞች በህይወት የተረፈ ሰው አለላገኙም ተብሏል
በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ግዛት በደረሰ የሄሊኮፕተር መከስከስ አደጋ ሁሉም ተሳፋሪዎች ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ ።
22 ሰዎችን አሳፍራ የነበረችው ሄሊኮፕተሯ በተከሰከሰችበት በሩሲያዋ ሩቅ ምስራቅ ግዛት ካምቻትካ የደረሱት የነፍስ አድን ሰራተኞች በህይወት የተረፈ ሰው አለማግኘታቸውን ሮይተርስ የሩሲያውን ታስ የዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።
ኤም-አይ 8ቲ የተባለችው ሄሊኮፕተር የተነሳችው በቫችካዜት እሳተገሞራ አቅራቢያ ከሚገኘው የጦር ሰፈር ነበር።
ከሞስኮ ሰባት ሺ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ካምቻትካ በሳምንቱ መጨረሻ ዝናብ እና ንፋስ በቀላቀለ አውሎንፋስ ተመታለች። ነገርግን አውሎንፋሱ አደጋው እንዲከሰት ምክንያት ስለመሆኑ አልታወቀም።
ሄሊኮፕተሯ በተከሰከሰችበት ቦታ እስካሁን በተካሄደ ፍለጋ የ17 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ቢቢሲ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል። ይህ አይነቱ አደጋ ህዝብ ተራርቆ በሚኖርበት የሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ግዛት በአንጻራዊት በተደጋጋሚ ይከሰታል።
ከሶስት አመታት በፊት ቱሪስቶችን አሳፍራ የነበረች ሄሊኮፕተር ካምቻትካ በሚገኝ ሀይቅ ውስጥ ተከስክሳ የስምንት ሰዎች ህይወት አልፏል።
ባለፈው ቅዳሜ ከግንኙነት ራዳር ውጭ ሆና የነበረችው ሄሊክፕተር 19 ጎብኝዎችን እና ሶስት ሰራተኞችን ይዛ ነበር። የሄሊኮፕተሯ ስብርባሪ እሁድ ጠዋት በተራራማ አካባቢ መገኘቱን የካምቻትካ ገዥ ቭላድሚር ሶሎዶቭ ተናግረዋል።
በሩሲያ የአደጋ ጊዜ ሚኒስቴር ቴሌግራም ገጽ የተለቀቀው ቪዲዮ የሄሊኮፕተሯ ስብርባሪ በደን ከተሸፈነ ተራራ ስር ወድቆ አሳይቷል። ባለስልጣናት እንዳሉት ስብርባሪው የተገኘው ሄሊኮፕተሯ ከግንኙነት ውጭ በሆነችበት ቦታ አቅራቢያ ነው።
ከሚኒስቴሩ የመጡት ኢቫን ለሚኮቭ እስካሁን የ17 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን እና ሌሎቹን ለማግኘት ፍለጋው መቀጠሉን ገልጸዋል።
ሄሊኮፕተሯ ንብረትነቷ የጎብኝዎችን በረራ የሚያመቻቸው መቀመጫውን ካምቻትካ ያደረገው ቪታይዝ-አይሮ የተባለው ኩባንያ ነው።