በኬንያ አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ በተከሰተ የእሳት አደጋ የ17 ተማሪዎች ህይወት አለፈ
በአደጋው የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል የገለጸው ፖሊስ 13 ሰዎች ጉዳት እንደደረሳባቸው አስታውቋል
ከ20 አመት በፊት በኬንያ በተመሳሳይ በደረሰ አደጋ 67 ተማሪዎች መሞታቸው ይታወሳል
በማከላዊ ኬንያ በአዳሪ ትምህርት ቤት በተማሪዎች ማደርያ ውስጥ በተቀሰቀስ እሳት የ17 ተማሪዎች ህይወት አለፈ፡፡
ሂልሳይድ ኢንዳርሻ በተባለ የመጀመርያ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት የተከሰተው እሳት መንስኤ ላይ ምርመራዎች እየተደረጉ መሆኑን የገለጸው ፖሊስ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቃብ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
በአደጋው ህይወታቸው ካለፈው ተማሪዎች ባለፈ 13 ሰዎች ከፍተኛ ቃጠሎ ደርሶባቸው ሆስፒታል ውስጥ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አደጋውን አስከፊ እና አሳዛኝ ሲሉ ገልጸውታል፤ በአደጋው መንስኤ ዙርያም አፋጣኝ ምርመራ እንዲጀመር አዘዋል፡፡
በተጨማሪም ለእሳት አደጋው መከሰት ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰቦች ለፍርድ እንደሚቀርቡ ነው ያስታወቁት፡፡
የፖሊስ ቃል አቀባይ ርሲላ ኦንያንጎ በአደጋው ህይወታቸው ያለፉ ተማሪዎች ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ በቃጠሎው እንደተጎዱ ተናግረዋል፡፡
የኬንያ ቀይ መስቀል ማህበር በአደጋው ድንጋጤ እና ሀዘን ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች እና መምህራን ከሚገኙበት የስነልቦና ጫና እንዲያገግሙ የሀዘን ጊዜ ማማከር አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ሂልሳይድ ኢንዳርሻ የተባለው የመጀመርያ ደረጃ የግል አዳሪ ትምህርት ቤት ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ በሰሜናዊ አቅጣጫ 150 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡
ትምህርት ቤቱ እድሚያቸው ከ5-12 የሚደርሱ ህጻናት ተማሪዎችን የሚያስተምር እንደሆነም ታውቋል፡፡
በኬንያ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚከሰቱ የአሳት አደጋዎች በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ሲሆን በ2017 በዋና ከተማዋ በሚገኝ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት በተፈጠረ አደጋ የ10 ተማሪዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡
በተመሳሳይ ከ20 አመት በፊት በደቡብ ምስራቅ ናይሮቢ በደረሰ ቃጠሎ 67 ተማሪዎች ሲሞቱ በሀገሪቱ ታሪክ አስከፊው የእሳት አደጋ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡