የ42 ሴቶችን ህይወት ያጠፋው ኬንያው በፖሊስ ተያዘ
ከሰሞኑ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ የ9 ሴቶችን አስክሬን በቆሻሻ መጠያ ውስጥ ያገኝው ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አውሏል
በኬንያ ዋና ከተማ በተፈጸመው ወንጀል ግለሰቡ ከ2022 ጀምሮ ባለቤቱን ጨምሮ 42 ሴቶችን መግደሉን አምኗል
በኬንያ የ42 ሴቶችን ህይወት የቀጠፈው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ባሳለፍነው አርብ በኬንያ ዋና ከተማ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ የ9 ሴቶች የተቆራረጠ አካል በቆሻሻ መጣያ ስፍራ መገኝቱን ተከትሎ ፖሊስ ወንጀለኛውን ለመያዝ ምርመራ እና ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ጆማይሲ ካሊሲያ የተባለው የ33 አመት ኬንያዊ የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ እየተመለከተ በሚገኝብት ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ከ2022 ጀምሮ ባለቤቱን ጨምሮ የ42 ሴቶችን ህይወት ማጥፋቱን ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ግለሰቡ ለመጨረሻ ጊዜ ከገደላቸው ሴቶች መካከል ከአንዷ ጋር ባደረገው የሞባይል ገንዘብ ልውውጥ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ሊያዝ ችሏል፡፡
የናይሮቢ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ሃላፊ ሞሀመድ አሚን እንደተናገሩት ግለሰቡ አስክሬኖቹ ከተገኙበት አካባቢ 100 ሜትር ርቀት ላይ የሚኖር ሲሆን ፖሊስ በመኖርያ ቤቱ ውስጥ ባደረገው ፍተሻ 10 ሞባይል ስልኮችን ፣ ላፕቶፕ ፣ የሴቶች አልባሳት እና መታወቂያዎችን አግኝቷል፡፡
በተጨማሪም የተለያየ መጠን ያላቸው የስለት መሳርያዎች እና የሟቾችን አስክሬን ከቆራረጠ በኋላ የሚጥልባቸውን በርካታ ከረጢቶች እንደተገኙ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ሟቾቹ ከ18 እስ 30 እድሜ የሚጠጉ ሴቶች ሲሆኑ ሁሉም የተገደሉበት መንገድ አንድ አይነት መሆኑ ነው የተሰማው፡፡
ፖሊስ ግለሰቡ ግድያውን በምን ምክንያት እንደሚፈጽም ለማወቅ ተጨማሪ ምርመራዎችን በማከናወን ላይ ሲሆን በነገው እለት ተጠርጣሪውን ለፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ ይፋ አድርጓል፡፡
ከዚህ ባለፈ አስክሬኖቹ የተገኙበት ስፍራ ለፖሊስ ጣቢያ ካለው ቅርበት አኳያ የጣቢያው ፖሊሶች ላይም በቀጣይ ተጨማሪ ምርመራዎች እንደሚደረጉ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ሃላፊው ሞሀመድ አሚን ተናግረዋል፡፡