የኬንያ ፖሊስ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይደረግ ከለከለ
ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፎችን የመከልከል መብት የለውም ያሉት ሰልፈኞች በዛሬው እለት በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግስት አቅራቢያ ተቃውሞ ለማሰማት ቀጠሮ ይዘዋል
ፕሬዝዳንት ሩቶ ተቃውሞ ያስነሳውን የፋይናንስ ህግ ሽረው የተለያዩ ማሻሻያዎችን ቢያደርጉም ህዝባዊ ተቃውሞው ግን አሁንም አልበረደም
የኬንያ ፖሊስ በማዕከላዊ ናይሮቢ እና በአጎራባች አካባቢዎች የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችን ከለከለ፡፡
የታክስ ጭማሪን ገቢራዊ የሚያደርገው የፋይናንስ ህግ መውጣቱን ተከትሎ በኬንያ የተቀጣጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ሩቶ ተቃውሞ የቀሰቀሰውን ህግ በመሻር ካቢኔያቸውን ሙሉ ለሙሉ ከስራ አሰናበተው ተጨማሪ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ቃል ቢገቡም የፕሬዝዳንቱን ከስልጣን መነሳት የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች በተከታታይ በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡
የሰላማዊ ሰልፈኞቹን እና የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ ተቸግርያለሁ ያለው የሀገሪቱ ፖሊስ ከዛሬ ጀምሮ ሰላማዊ ሰልፎች በማዕከላዊ ናይሮቢ እና በዙርያው በሚገኙ አካባቢዎች እንዳይደረጉ ከልክሏል፡፡
በዛሬው እለት ሰልፈኞች በኡህሩ ፓርክ ተሰባስበው ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግስት በማቅናት ተቃውሟቸውን ለማሰማት እቅድ ይዘዋል፡፡
የሀገሪቱ ተጠባባቂ የፖሊስ አዛዥ ዳግላስ ካንጃ ሰላማዊ ሰልፎቹ መሪ ስለሌላቸው ወደ አመጻ እየተቀየሩ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ስለማይቻል ተጨማሪ መመሪያዎች እስከሚተላለፉ ድረስ ሰልፍ ማካሄድ ተከልክሏል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች በርካታ የንግድ እንቅስቃሴ በሚከናወንበት ማዕከላዊ ናይሮቢ ሰልፉን በመጠቀም ወንጀሎችን ለመፈጸም ስለመዘጋጀታቸው ፖሊስ መረጃ እንደደረስው ገልጸዋል፡፡
ሰለማዊ ሰልፎችን ማካሄድ ህገ መንግስታዊ መብታችን ነው ያሉት ኬንያውያን ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፍ የመከልከል መብት የለውም በሚል ለዛሬ የያዙት የተቃውሞ ፕሮግራም እንደሚቀጥል በማህበራዊ ትስስር ገጾች መረጃዎችን እየተለዋወጡ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ሩቶ ከስልጣን እስካልተነሱ ድረስ ተቃውሞውን እንቀጥላለን የሚሉት ሰልፈኞቹ በሰልፉ ላይ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ፖሊስ ተጠያቂ እንዲደረግ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
የኬንያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መረጃ መሰረት ለሳምንታት በቀጠሉት ሰልፎች እሳከሁን 50 ሰዎች ሲገደሉ 413 ሰዎች ደግሞ ቀላል እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡