ኢትዮጵያን ጨምሮ 172 ሀገራት ከኮሮና ክትባቶች አምራች ተቋማት ጋር የተፈጠረውን ጥምረት ተቀላቅለዋል
ከ172ቱ ሃገራት መካከል 80ዎቹ የራሳቸውን ወጪ ሊሸፍኑ የሚችሉ ናቸው
ጥምረቱ የክትባቶቹን ፍትሃዊ ተደራሽነትና ስርጭት ለማረጋገጥ የተፈጠረ ነው
ኢትዮጵያን ጨምሮ 172 ሀገራት ከኮሮና ክትባቶች አምራች ተቋማት ጋር የተፈጠረውን ጥምረት ተቀላቅለዋል
172 የዓለማችን ሃገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ፍትሃዊ ተደራሽነትና ስርጭትን ለማረጋገጥ የተዘረጋውን መርሃግብር (COVAX) መቀላቀላቸውን ዓለም አቀፉ የክትባቶች ትብብር (ጋቪ) አስታውቋል፡፡
ከሃገራቱ መካከል 92ቱ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሲሆን 80ያዎቹ የክትባቱን ወጪ በራሳቸው ለመሸፈን የሚያስችል ዐቅም ያላቸው ሲሆኑ እስከያዝነው ወር (ነሃሴ) መጨረሻ ወጪያቸውን እንደሚሸፍኑ እንዲያረጋግጡ እና እስከ መስከረም 8 ድረስ (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ውለታ ገብተው ቅድመ ክፍያ እንዲፈጽሙ ዕቅድ ተይዞላቸዋል፡፡ ብዙዎቹም በዚህ ረገድ ያላቸውን ፍላጎት ቀድመው አሳውቀዋል፡፡
የታሰበው መዋጮ የሚሳካ ከሆነም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ምጣኔ ሃብት ካላቸው ኢትዮጵያን መሰል 92 ሃገራት ጋር ተቀናጅተው ማረጋገጫ አግኝተው የሚመረቱ ክትባቶችን ለህዝባቸው የሚያደርሱ ይሆናል፡፡
ዝቅተኛ እና መካከለኛ ምጣኔሃብት ያላቸው 92ቱ ሃገራት ክትባቱን ከ3 ዶላር ባልበለጠ የግዢ ዋጋ ሊያገኙ የሚችሉበት አዲስ የፋይናንስ አሰራር ስርዓት (COVAX AMC) ተዘርግቷል፡፡
አዲስ በተዘረጋው ስርዓት እስከ 2 ቢሊዬን ዶላር ለማሰባሰብ የታሰበም ሲሆን እስካሁን ከ600 ሚሊዬን ዶላር በላይ ገንዘብን ለማሰባሰብ ስለመቻሉ ነው የተገለጸው፡፡
መቶ ሚሊዬን የሚደርሱ የአስትራዜናካ እና የኖቫቫክስ ክትባቶችን ለማምረት የሚያስችል ድጋፍ በCEPI እና በቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ትብብር መገኘቱም ተገልጿል፡፡
ሆኖም አዲስ በተዘረጋው ስርዓት እስከተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ለማሰባሰብ የታቀደው 2 ቢሊዬን ዶላር ነው፡፡ ይህ አሁንም የተሻለ ምጣኔ ሃብትን ለመገንባት የቻሉ ሃገራት እና በጎ አድራጊ ተቋማት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው፡፡
የ172ቱ ሃገራት ስብስብ ከአጠቃላይ የዓለማችን ህዝብ ብዛት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው፡፡
ሁሉም አህጉር በስብስቡ ውስጥ ተወክሏል እንደ ጋቪ መረጃዎች፡፡ ከቡድን 20 አባል ሃገራት ግማሽ ያህሉ የስብስቡ አካልም ናቸው፡፡
መርሃ ግብሩ ከክትባት አምራች ተቋማት ጋር በመተባበር ፍትሃዊ ተደራሽነትና ስርጭትን ለማረጋገጥ ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከወረርሽኝ ዝግጁነት ጥምረት (CEPI) ጋር በቅንጅት የሚሰራ ነው፡፡
አ.ኤ.አ እስከ 2021 መጨረሻ 2 ቢሊዬን የሚደርሱ ክትባቶችን ለተጠቃሚዎች የማድረስ ዐቅድም አለው፡፡
ቶሎ ሊደርሱ እንደሚችሉ በታመነባቸው 9 እጩ ክትባቶች የምርምር እና የምርት ሂደቶች በመስራትም ላይ ይገኛል፡፡
ሌሎች 9 ተጨማሪ ክትባቶችን በመገምገም ሂደት ላይ መሆኑን ያስታወቀም ሲሆን ከግዙፍ መድሃኒት አምራች ተቋማት ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
ባሳለፍነው ሰኔ ከብሪታኒያው አስትራዜናካ ጋር ያደረገው ስምምነት ተጨማሪ 3 መቶ ሚሊዬን ክትባቶችን ለማግኘት የሚያስችልም ነው፡፡
እስካሁን የተለያዩ ተቋማትንና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበር 1 ነጥብ 4 ቢሊዬን ዶላር ገንዘብን ለማሰባሰብ የቻለም ሲሆን አሁንም ተጨማሪ አንድ ቢሊዬን ዶላር እንደሚያስፈልገው አስታውቋል፡፡