ተደጋግመው ከሚፈጸሙት ጥቃቶች መካከል የአጥፊ ሶፍትዌሮች (ማልዌር) ጥቃት ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛል
በተያዘው ዓመት በኢትዮጵያ 1 ሺ 78 የሳይበር ጥቃቶች ተቃጥተዋል
በተያዘው ዓመት በኢትዮጵያ የተለያዩ ተቋማት ላይ ከተቃጡ 1 ሺ 78 የሳይበር ጥቃቶች 787 ያህሉን ማክሸፉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) አስታወቀ፡፡
ከተቃጡት ጥቃቶች 73 በመቶ ያህሉን ለማክሸፍ ተችሏል ያሉት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ከፍያለው ተፈራ 124 ምላሽ በመሰጠት ሂደት ላይ እንደሚገኙ እና ቀሪዎቹ 167 የሚሆኑ ጥቃቶች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ አመት 474 የአጥፊ ሶፍትዌሮች (ማልዌር)፣ 288 የድረ-ገፅ ፣104 የመሠረተ-ልማት ቅኝት፣ 188 ወዳልተፈቀደ ሲስተም ሰርጎ የመግባት፣ 22 የሳይበር መሠረተ-ልማቶችን ሥራ የማቋረጥ እና 2 በሳይበር የማጭበርበር ጥቃቶች ተፈጽመዋል እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡
ጥቃቶቹ የሃገሪቱን ቁልፍ መሰረተ-ልማቶችን እና ተቋማትን ኢላማ አድርገዉ የተፈጸሙም ናቸው፡፡
ካለፉት አመታት ጋር ሲነጻጸር የሚሰነዘረው ጥቃት የቁጥር ጭማሬ አሳይቷል ያሉት አቶ ከፍያለው በኤጀንሲው የሳይበር ጥቃት አደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ መስጫ ዲቪዥን (Ethio-CERT) የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ ለማክሸፍ መቻሉን ተናግረዋል።
ሆኖም ከተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለጥቃቶቹ አጥጋቢውን ምላሽ ለመስጠት አዳጋች ሆኗል፡፡
ለምን አዳጋች ሆነ የጥቃቱስ ቁጥር ለምን ጨመረ?
የተለያዩ የሀገሪቱ ተቋማት ወደ ዲጂታል አለም በስፋት እየገቡ ነው፡፡ ይህንንም የኤጀንሲውና ሌሎችም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሆኖም ተቋማቱ ስለ ሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ ጉዳዮች የተሻለ የግንዛቤን አለመያዛቸው እና የዝግጁነት ደረጃቸው ማነሱ በተለያዩ አካላት ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች ተጋላጭ አድርገዋቸዋል፡፡
የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆንን በምክንያትነት የሚጠቅሱት አቶ ከፍያለው ግለሰቦች መሰረታዊ የተባሉ የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂን አለመተግበር፣ ህጋዊ ያልሆኑ (Cracked) ሶፍትዌሮች መጠቀም፣ ተቋማት የኮምፒውተር ስርዓቶቻቸዉን (ሲሰተሞቻቸውን) የሳይበር ደህንነት አለማስፈተሽ ለጥቃቱ መጨመር ምክንያት ናቸው ይላሉ፡፡
“ጥቃት የደረሰበት ተቋም ቋሚ አድራሻ አለመታወቅ፣ አይፒ (የኢንተርኔት አሃዛዊ አድራሻ) የሚለዋወጥ መሆን፣ተቋማት መረጃው ከተሰጣቸው በኋላ ቸልተኝነት ማሳየት፣በአለም አቀፍ ደረጃ በኢንዱስትሪው አዳዲስና ውስብስብ የሆኑ ጥቃቶች መፈጠራቸው እንዲሁም በተቋማትና በግለሰብ ደረጃ የሳይበር ደህንነት እውቀት ግንዛቤ ማነስ” ከተፈጠሩት የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ ምላሽ ለመስጠት አስቸጋሪ ካደረጋቸው መካከል እንደ ዋነኛ ምክንያቶች የሚጠቀሱ መሆናቸውንም ያስቀምጣሉ።
የሚፈጸሙት የሳይበር ጥቃቶች ምን ዓይነት ናቸው?
በከፍተኛ መጠን የተፈጸመዉ የሳይበር ጥቃት ዓይነት በማልዌሮች የተፈጸሙ ጥቃቶች መሆናቸዉን የገለጹት አቶ ከፍያለው ጥቃቶቹ በተለያዩ መንገዶች የሚፈጸሙ መሆናቸዉን ጠቅሰዋል፡፡
Ransomware (አጋች ማልዌር) የማልዌር ጥቃት ከሚፈጸምባቸው ስልቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ መረጃን በርብረው የሚመነትፉ የተለያዩ ፋይሎችን በማገት ለማስፈታት ገንዘብ የሚጠይቁበት አንዱ መንገድ ነዉ፡፡
ከጀርባ ሆኖ ተጠቃሚው ሳያውቅ የሲስተሙን ሪሶርስ ለራሳቸው የሚመዘብሩበት Cryptocurrency miner (ክሪፒቶ ከረንሲ ማይነር) ሌላኛው የማልዌር ጥቃት ዓይነት ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም የመረጃ መዝባሪዎች ጥቃት ለማድረስ Bot malware (ቦት ማልዌር) የሚባለዉን እና የሳይበር አጥቂዎች የግለሰቦችን ኮምፒውተር በመቆጣጠር ሌሎችን ለማጥቃት በሚጠቀሙበት ስልት ይገለገላሉም ብለዋል፡፡
“90 በመቶው ጥቃት በግንዛቤ ጉድለት የሚከሰት ነው”
“90 በመቶው የሚሆነው የሳይበር ጥቃት በግንዛቤ ጉድለት የሚከሰት ነው” ያሉም ሲሆን ኤጀንሲው ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ለተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት የሳይበር ደህንነት ስልጠናዎችን መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
ማህበረሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣዉ የሳይበር ጥቃት እንዳይጋለጥ የጥንቃቄ ርምጃዎችን በተገቢዉ መንገድ በመተግበር በግለሰብ፣በተቋም እና በሃገር ላይ ሊደርሱ የሚችሉ የሳይበር ጥቃት አደጋዎች ሊቀንስ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡