በግጭቱ በአስሮች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን የግዛቱ አስተዳዳሪ ገልጸዋል
በሱዳን ደቡብ ዳርፉር ግዛት በሪዜይጋት እና ፈላታ ጎሳዎች መካከል ትናንት ሰኞ ዕለት ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም ግጭት መቀስቀሱን የሱዳን ዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
በአካባቢው አንድ እረኛ መገደሉን ተከትሎ በሁለቱ ጎሳዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በአስሮች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን የደቡብ ዳርፉር አስተዳዳሪ ሙሳ ማህዲ ገልጸዋል፡፡
ከእረኛው ግድያ ጋር ተያይዞ ከደቡብ ዳርፉር ዋና ከተማ ንያላ 85 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አል ጣዊል መንደር ፣ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ነው ሰዎች የተገደሉት እና የቆሰሉት፡፡
ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ግጭቱ ወደተከሰተበት አካባቢ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይሎች መላካቸውንም የግዛቱ አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡
በአንድ በኩል በፈላታ እና በማሳሊት ጎሳዎች ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በፈላታ እና በሪዜይጋት ጎሳዎች መካከል ከአንድ ወር በፊት ግጭቶች መከሰታቸውን ተከትሎ የደቡብ ዳርፉር ግዛት ወደ ስፍራው በርካታ ወታደሮችን ልኮ እንደነበር ዘገባው ያመለክታል፡፡
ከሦስት ቀናት በፊት ጥር 08 ቀን 2013 ዓ.ም በሱዳን የምዕራብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ አል ጂኔይና ፣ አረብ ነን በሚሉ እና አረብ አይደለንም በሚሉ በሁለት ጎሳዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ደግሞ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 129 መድረሱ ትናንት ተገልጿል፡፡
የዳርፉር አካባቢ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ያለበት ሲሆን በአካባቢው የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ሕብረት ጥምር የሰላም አስከባሪ ኃይል ፣ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ተልዕኮውን አጠናቆ መውጣት ጀምሯል፡፡ ይህም አካባቢውን ለሌላ ቀውስ እንዳይዳርግ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ለዓመታት በቆየው የዳርፉር ግጭት እና የሀር ማጥፋት ወንጀል ከ 300,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል፡፡