24 ሀገራት በሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ እስካሁን 18 ሀገራት ማጣሪያውን አለፉ
ካሜሩን ለምታስተናግደው የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተካሄዱ ነው
ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዋን በነገው እለት በኮትዲቮር ታካሂዳለች
በካሜሩን በሚካሄደው የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች በመካሄድ ላይ ሲሆኑ ትናንት ሱዳን ከደቡብ አፍሪካ ባካሄዱት የማጣሪያ ጨዋታ ሱዳን 2 ለ 0 በማሸነፍ ከምስራቅ አፍሪካ ቀድማ ያለፈች ሀገር መሆን ችላለች፡፡
ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰቸው ሱዳን ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፈችው በ2012 የውድድር ዓመት ሲሆን ለሩብ ፍፃሜ ደርሳ ነበር።
እስካሁን በተደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ሱዳንን ጨምሮ ሞሮኮ፤ናይጀሪያ፤ኮቲዲቯር፤ ካሜሩን፤ኢኳቶሪያል፣ጊኒ፤ግብጽ፤ኮሞሮስ፤ማሊ፤አልጀሪያ፤ጋቦን፤ሴኔጋል፤ዚምባብዌ፤ቡርኪናፋሶ፤ጋምቢያ፤ጋና፤ጊኒ፤ እና ቱኒዝያ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ናቸው።
በዚህ ውድድር ላይ የ24 ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉ ሲሆን ቀሪ ስድስት ሀገራት ዛሬ እና ነገ በሚያደርጉት የማጣሪያ ጨዋታዎች አላፊዎቹ ሀገራት እንደሚታወቁ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረገጹ አስታውቋል።
ወደ ውድድሩ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ከሚያካሂዱ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 ሀገራት ዛሬ እና ነገ የማጣሪያ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የዘንድሮውን የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዋን ከኮትዲቮር ጋር ለማካሄድ ወደ ስፍራው ያቀናች ሲሆን ነገ አመሻሽ እንደምታካሂድ ይጠበቃል።
ውድድሩ በካሜሩን አምስት ከተሞች ከሰኔ 18 እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ሀገሪቱ ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀች አስታውቃለች።
አንጎላ፤ ቦትስዋና፤ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ኢስዋትኒ፤ኬንያ፤ሌሴቶ፤ሊቢያ፤ናሚቢያ፤ኒጀር፤ ደቡብ ሱዳን፤ ታንዛንያ፤ እና ዛምቢያ ወደ ዘንደሮው ውድድሩ መውደቃቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ሲሆኑ ቻድ በውድድሩ እንዳትሳተፍ የታገደች ሀገር ነች።
ሶማሊያ እና ኤርትራ በማጣሪያው ውድድር ላይ ያልተሳተፉ ሀገራት ሲሆኑ ጅቡቲ፤ላይቤሪያ፤ሲሸልስ እና ሞሪሺየስ በቅድመ ማጣሪያ ውድድር ላይ የተሰናበቱ አገራት ናቸው።
የአፍሪካ ዋንጫን ግብጽ ለ7 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ አገር ስትሆን ካሜሩን 5 ጊዜ ጋና 4 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚዎቹ አገራት ናቸው።
በ2019 በግብጽ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ አልጀሪያ ከሴኔጋል ለፍጻሜ ደርሰው አልጀሪያ ዋንጫ ማንሳቷ ይታወሳል።