“አፍሪካዊ ብሄራዊ ቡድን በቅርቡ የዓለም ዋንጫን ማንሳት አለበት” አዲሱ የካፍ ፕሬዝደንት
ካሜሮን በ1990፣ ሴኔጋል በ2002 እንዲሁም ጋና በ2010 በዓለም ዋንጫ ለሩብ ፍጻሜ መድረስ ችለዋል
በ4 ዓመት ቆይታቸው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ካልቻሉ ስልጣናቸውን እንደሚለቁ የካፍ መሪ ፓትሪስ አስታውቀዋል
አፍሪካዊ ብሄራዊ ቡድን በቅርቡ የዓለም ዋንጫን ማንሳት መቻል አለበት አሉ ፤ አዲሱ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን /ካፍ/ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ሞትሴፔ።
በዓለም ዋንጫ የአፍሪካን አህጉር ወክለው የሚወዳደሩ ብሄራዊ ቡድኖች ከተቻለ በቀጣዩ ዓለም ዋንጫ አሊያም ቀረብ ባለ ጊዜ የዓለም ዋንጫን እንዲያነሱ ማድረግ እቅዳቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ከሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ የሚሰሩ መሆኑንም ፓትሪስ ሞትሴፔ መግለጻቸውን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን አስነብቧል።
በዓለም ዋንጫ እስካሁን ከሩብ ፍጻሜ ማለፍ የቻለ አፍሪካዊ ሀገር የሌለ ሲሆን፣ ካሜሮን በ1990፣ ሴኔጋል በ2002 እንዲሁም ጋና በ2010 ለሩብ ፍጻሜ መድረስ ችለዋል።
የካፍ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ሞትሴፔ እቅዳቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፣ በ4 ዓመት ቆይታቸው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ካልቻሉም ስልጣናቸውን እንደሚለቁ አስታውቀዋል።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ /ፊፋ/ የአፍሪከ ዋንጫ በ4 ዓመት አንዴ እንዲካሄድ ጥሪ ቢያቀርብም፣ ፓትሪስ ሞትሴፔ ግን በስልጣን ቆይታቸው የአፍሪካ ዋንጫ በ2 ዓመት ልዩነት መካሄዱን ይቀጥላል ብለዋል።
ቢሊየነሩና የማሜሎዲ ሰንዳውን ክለብ ባለቤት ፓትሪስ ሞትሴፔ ባሳለፍነው ሳምንት የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።