በአስር ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውድድር ዛሬ መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ ተጠናቋል
አንድ ጨዋታ እየቀረው የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮንነቱን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር የመጨረሻ ጨዋታውን በማድረግ ዋንጫውን አንስቷል፡፡
በጨዋታው ሻምፒዮኑ ቡድን በሎዛ አበራ ሁለት ጎሎች 2 ለ 1 ተጋጣሚውን የረታ ሲሆን ቡድኑ በውድድር ዘመኑ 46 ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል፡፡
በአስር ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውድድር ዛሬ መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሁለቱ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ሎዛ አበራ በ17 ጎሎች የውድድር ዘመኑ ኮከብ ጎል አግቢ መሆን የቻለች ሲሆን፣ ሌላዋ የቡድኑ ተጫዋች ረሂማ ዘርጋው በ16 ጎሎች ሁለተኛ ኮከብ ጎል አግቢ በመሆን ከማጠናቀቋም በላይ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብላ ተሰይማለች፡፡ የቡድኑ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛውም ኮከብ አሰልጣኝ ሆኖ ተመርጧል፡፡ የመከላከያዋ ታሪኳ በርገና ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆናለች፡፡
ኮከቦቹ ዛሬ ይፋ ቢደረጉም ሽልማታቸውን በቀጣይ ይረከባሉ። ሎዛ አበራ እና ሰናይት ቦጋለ ከሦስት ክለቦች ጋር በተከታታይ ለአምስት ዓመታት የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ታሪክ ሰርተዋል፡፡
ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ በተካሄደውና ዛሬ ፍጻሜውን ባገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር መከላከያ በ39 ነጥብ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ በ36 ነጥብ 2ኛና 3ኛ በመሆን የውድድር ዘመኑን ያጠናቀቁ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫን ማግኘት ችሏል፡፡