እስሩ ኒውክሌር በታጠቀች ሀገር ውስጥ አዲስ ብጥብጥ ሊያስነሳ እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል
የፓኪስታን ጸረ-ስርቆት ቡድን የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራን ካንን በእስላማባድ በቁጥጥር ስር አውሏል።
እስሩ ኒውክሌር በታጠቀች ሀገር ውስጥ አዲስ ብጥብጥ ሊያስነሳ እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል።
የካን ፓርቲ በመላ ሀገሪቱ የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያደርግ የሁከት መቆጣጠሪያ የለበሱ በርካታ የጸጥታ ኃይሎች የቀድሞን ጠቅላይ ሚንስትር በቁጥጥር ስር ሲያውሉ የሚያሳይ ምስል ይፋ ሆኗል።
ፓርቲው በትዊተር ገጹ "የፓኪስታን ሰዎች ሀገራችሁን የምትታደግበት ጊዜው አሁን ነው። ሌላ እድል አታገኙም" ብሏል።
እስሩ ፓኪስታናዊያን በአስርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ የምጣኔ-ሀብት ቀውስ ውስጥ ባሉበት ወቅት የመጣ ነው።
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ራና ሳናኡላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ካን በ"ብሄራዊ ተጠያቂነት ቢሮ" በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸው በቢሮው ጥሪ ተደርጎላቸው አልቀረቡም ብለዋል።
ሮይተርስ በተመለከተውና ከሳምንት በፊት በወጣው የእስር ማዘዣ ካን በሙስና እና ብልሹ አሰራር ወንጀል ተከሰዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ባለፈው ዓመት በፓርላማ በተሰጠ ድምጽ ከስልጣን ከተባረሩ ጀምሮ ከ100 በላይ ክሶች ቀርበውባቸዋል።
ካን ከአምስት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው አራቱን አገልግለዋል።
ኢምራን ካን ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ህዝባዊ ስልጣን እንዳይዙ የሚከለከል ሲሆን፤ ፓኪስታን ብሄራዊ ምርጫ በህዳር ወር ታካሂዳለች።