ፓኪስታን እና ኢራን ድንበር በማቋረጥ የፈጸሟቸው ጥቃቶች 900 ኪሎሜትር ድንበር የሚጋሩትን ሀገራት ውጥረት አባብሶታል
ፓኪስታን በኢራን በሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሀገሪቱን ከኢራን በሚያዋስነው ድንበር ሲስታን ባሉቺስታን በተባለው አካባቢ በተፈጸሙት የሚሳኤል ጥቃቶች ሶስት ሴቶችና አራት ህጻናት ህይወታቸው ማለፉን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ኢራናውያን አለመሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ቁጥራቸውን ያልጠቀሳቸው ሽብርተኞች መገደላቸውን ነው የገለጸው።
“ባሎቺስታን ነጻነት ግንባር” በተባለው ከፓኪስታን የመገንጠል ጥያቄ የሚያቀነቅን ቡድን ታጣቂዎች ላይ በጦር አውሮፕላን የተፈጸመው ጥቃት የኢራንን ሉአላዊነት የተዳፈረ አለመሆኑንም ጠቁሟል።
የአየር ጥቃቶቹ የታጣቂዎቹ መደበቂያ ስፍራዎች መመታታቸውን የጠቀሰው የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በንጹሃን ላይ ስለደረሰው ጉዳት ማብራሪያ አልሰጠም።
ኢራንም ኢስላማባድ በግዛቷ ስለፈጸመችው ጥቃት እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።
ኢራን ከሁለት ቀናት በፊት በፓኪስታን በሚገኙ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ባላቸው ታጣቂዎች (ጃይሽ አል አድል) ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን መግለጿ ይታወሳል።
በዚህ ጥቃትም ሁለት ህጻናት ህይወታቸው ማለፉና የአየር ክልሏ መጣሱ ያስቆጣት ኢስላማባድ ለደረሰው ጉዳት ቴህራን ሃላፊነቱን ትወስዳለች ማለቷን ሬውተርስ ዘግቧል።
ፓኪስታን በትናንትናው እለትም በኢራን የሚገኙትን አምባሳደሯን የጠራች ሲሆን ከቴህራን ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ማቋረጧን ገልጻለች።
900 ኪሎሜትር የሚረዝም ንበር የሚጋሩት ፓኪስታን እና ኢራን በድንበር አካባቢ በሚፈጸሙ ጥቃቶች በተደጋጋሚ እርስ በርስ ሲካሰሱ የቆዩ ሲሆን፥ የሰሞኑ ጥቃትም የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ እንዳያሻክረው ተሰግቷል።