የመንግስታቱ ድርጅት “በአማራ ክልል ግጭት ከ180 በላይ ሰዎች ተገድለዋል” አለ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች መታሰራቸውንም በድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ገልጿል
ተመድ በክልሉ እየተዋጉ የሚገኙት ሁለቱም ሃይሎች ግጭት እንዲያቆሙ ጠይቋል
በአማራ ክልል ከሃምሌ ወር ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት በጥቂቱ 183 ሰዎች መገደላቸውን የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ።
በድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ቃል አቀባዩዋ ማርታ ሁርታዶ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፥ በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ነው ብለዋል።
ድርጅቱ ባሰባሰበው መረጃ መሰረትም ከ180 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል ነው ያሉት።
የፌደራሉ መንግስት በነሃሴ ወር መግቢያ ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎም በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን አብራርተዋል።
“በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች ደርሰውናል፤ ከታሳሪዎቹ ውስጥ አብዛኞቹ የአማራ ማንነት ያላቸውና የፋኖ ደጋፊ ይሆናሉ ተብለው የተጠረጠሩ ናቸው” ሲሉም ገልጸዋል።
ቤት ለቤት የሚደረግ ፍተሻውም ከነሃሴ ወር ጀምሮ እየተጠናከረ ስለመሄዱ ነው ቃል አቀባዩዋ ያነሱት።
“ባለስልጣናት የጅምላ እስርን እንዲያቆሙና ከህግ አግባብ ውጭ የታሰሩ ዜጎችን እንዲፈቱ እንጠይቃለን” ያሉት ማርታ ሁርታዶ፥ የዜጎች ሰብአዊ መብት እና ነጻነት እንዲከበር አሳስበዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት “ሁሉም ወገኖች ግድያ እና የሰብአዊ መብት ጥሰትን እንዲያቆሙ” ጥሪ ማቅረቡንም በጄኔቫው መግለጫቸው ተናግረዋል።
የክልል ልዩ ሃይሎችን የማፍረስና በተለያዩ መደበኛ አደረጃጀት የማዋቀር ውሳኔ በፌደራሉ መንግስት ከተላለፈ በኋላ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።
ባለፈው ወርም የፋኖ ታጣቂዎች የተለያዩ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ካሳወቁ በኋላ የፌደራሉ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ከተሞቹንም ማስለቀቁን ማሳወቁ ይታወሳል።
በግጭቱ በርካታ ንጹሃን ስለመገደላቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ባወጣቸው መግለጫዎች አመላክቷል።