አምስት ሀገራት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው የጸጥታ መደፍረስ አሳስቦናል አሉ
ሀገራቱ ሁሉም ወገኖች ንጹሀን ዜጎችን እንዲጠብቁና ሰብዓዊ መብትን እንዲያከብሩ ጠይቀዋል
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ዘላቂ መረጋጋት እንዲመጣ ድጋፉን ይቀጥላል ብለዋል
አምስት የምዕራባዊያን አጋራት በኢትዮጽያ የንጹሀን ሞትና አለመረጋጋት እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል።
አውስትራሊያ፣ ጃፓን፣ ኒውዝላንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና አሜሪካ ናቸው በአማራና ኦሮሚያ ክልልሎች የተቀሰቀሰው ግጭት አሳስቦናል ያሉት።
ሀገራቱ ሁሉም ወገኖች ንጹሀን ዜጎችን እንዲጠብቁና ሰብዓዊ መብትን እንዲያከብሩ እናበረታታለን ብለዋል።
ውስብስብ ጉዳዮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በጋራ እንዲፈቱም እንዲሁ።
ሀገራቱ በጋራ በሰጡት መግለጫ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ዘላቂ መረጋጋት እንዲመጣ ድጋፉን ይቀጥላል ብለዋል።
የፌደራል መንግስት ባለፈው ሚያዝያ ወር የክልል ልዩ ኃይሎችን ለማፍረስና መልሶ ለማደረጃት መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር እየተባባሰ መጥቷል።
በክልሉ የተነሳውን አለመረጋጋት በመደበኛ የጸጥታ መዋቅር መፍታት አልተቻለኝም ያለው መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አውጇል።
በመንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተቀሰቀው ግጭት ንጹሃን ሰዎች እንዲጎዱ እና የሀገር አቋራጭ ትራንፖርት እንዲስተጓጎል አድርጓል።
ለጠቅላይ ሚንስትሩ ተጠሪ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ፤ ስድስት ከተሞችን ከታጣቂዎች ስጋት ነጻ ማድረጉን አስታውቋል።
የተመድ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል እየተባባሰ የመጣው ሁኔታ በጽኑ እንደሚያሳስበው ገልጿል።