ሙሳ ፋኪ የግጭቱ ተሳታፊ አካላት ግጭት እንዲያቆሙና ወደ ውይይት እንዲመጡ አሳስበዋል
አፍሪካ ህብረት በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው ገለጸ።
የአፍሪካ ህብረት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ አማራ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው አስታውቋል።
ህብረቱ በመገለጫው አክሎም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት ጉዳቱን እየተከታተሉት እንደሆነም ገልጿል።
ሊቀመንበሩ አክለውም በአማራ ክልል ያለውን ወታደራዊ ፍጥጫ በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑንም አስታውቋል።
አፍሪካ ህብረት ለኢትዮጵያ ህገ መንግስታዊ ስርዓት፣ ሉዓላዊነት እና አንድነት ድጋፍ እንደሚያደርግም ህብረቱ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ አካላት ንጹሀንን ከጉዳት እንዲጠብቁ እና ግጭት እንዲያቆሙ ያሳሰቡት ሊቀመንበሩ ወደ ውይይት እንዲመጡ እና ችግራቸውን እንዲፈቱም አስጠንቅቋል።
ሙሳ ፋኪ አክለውም አፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ለሚደረጉ ውይይቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥት የክልል ልዩ ሀይሎችን "መልሶ ማደራጀት" በሚል ከጀመረበት ካሳለፍነው ሚያዝያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል አለመረጋጋት ተከስቷል።
ይህ አለመረጋጋት ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎም የክልሉ መንግሥት ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ገልጾ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ባሳለፍነው ሰኞ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጽድቋል።