ከአንድሮይድ ስልኮች በፍጥነት መጥፋት ያለባቸው መተግበሪያዎች
ማልዌርፎክስ የተሰኘው የቴክኖሎጂ ኩባንያ 19 ከስማርት ስልኮች ላይ ሊጠፉ የሚገቡ አደገኛ መተግበሪያዎችን ይፋ አድርጓል
መተግበሪያዎቹ የባንክ አካውንት፣ የይለፍ ቃላት፣ የኢሜል መልዕክቶች እና ሌሎች ሚስጢራዊ መረጃዎችን ይመነትፋሉ ተብሏል
አንድሮይድ መተግበሪያዎችን እንዳሻን መጫን የሚያስችል ሶፍትዌር መሆኑ ለመረጃ መንታፊዎች የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው።
የሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች በፕሌይ ስቶር የተጫኑ መተግበሪያዎችን አውርደው ቫይረስ ከጫኑባቸው በኋላ በሌላ ስም ፕሌይ ስቶር ላይ ይጭኗቸዋል።
ለተለያየ አገልግሎት ይውላሉ በሚል ወይንም በድንገት የሚያወርዷቸው ሰዎችም በርካታ መረጃዎችን የያዙት ስልኮቻቸው በመረጃ ጠላፊዎቹ እጅ ይገባል።
በመተግበሪያዎች (አፕሊኬሽን) ውስጥ የሚገኙ ቫይረሶች በሶስት የሚመደቡ ናቸው።
“Harly Trojan”፣ “Joker” እና “Autolycos” ይሰኛሉ።
“Harly Trojan” በዋናነት በክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ መስለውና የክሬዲት ካርድ ቁጥር ጠይቀው የባንክ አካውንታችን ባዶ የሚያስቀሩ ናቸው፡፡
“Joker” ደግሞ የሚጠለፈውን ሰው የስልክ ቁጥር ዝርዝር፣ አጭር የጽሁፍ መልዕክቶችና ጠቅላላ የስማርት ስልኩን ባለቤት መረጃዎች ይሰበስባል፤ ያለባለቤቱ እውቅናም በገንዘብ የሚቀርቡ አገልግሎቶች ላይ አስመዝግቦ ወደ ጠላፊዎቹ ኪስ ያስገባል።
በ2021 በሺዎች የሚቆጠሩ አንድሮይድ ስማርት ስልኮችን ያጠቃው “Autolycos”ም ከታች በተዘረዘሩት መተግበሪያዎች (ከ14 - 19) በኩል የግለሰቦችን መረጃና ሚስጢራዊ ሰነዶች መመንተፉ ተነግሯል።
አንድሮይድ ስማርት ስልክ የምትጠቀሙ ሰዎች እነዚህን 19 አደገኛ መተግበሪያዎች ባለማወቅ ከጫናችኋቸው በፍጥነት አጥፏቸው ብሏል ማልዌርፎክስ የተሰኘው የቴክኖሎጂ ኩባንያ።
1. Fare Gamehub and Box
2. Hope Camera-Picture Record
3. Same Launcher and Live Wallpaper
4. Amazing Wallpaper
5. Cool Emoji Editor and Sticker
6. Simple Note Scanner
7. Universal PDF Scanner
8. Private Messenger
9. Premium SMS
10. Blood Pressure Checker
11. Cool Keyboard
12. Paint Art
13. Color Message
14. Vlog Star Video Editor
15. Creative 3D Launcher
16. Wow Beauty Camera
17. Gif Emoji Keyboard
18. Instant Heart Rate Anytime
19. Delicate Messenger
ጎግል ከፕሌይ ስቶር ላይ አንዳንዶቹን አደገኛ መተግበሪያዎች ቢያጠፋቸውም ስማቸውን በመጠኑ እየቀየሩ የሚሊየኖችን ደህንነት አደጋ ላይ የጣሉ በርካታ መተግበሪያዎች እንዳሉ ይነገራል።
እናም ከላይ የተዘረዘሩትን ጨምሮ የሚያጠራጥሩንና ተጠቅመንባቸው የማናውቀውን መተግበሪያዎች ማጥፋት ተገቢ ነው።
ፕሌይ ስቶር ላይ የትኛውንም መተግበሪያ ከመጫናችን በፊትም ሰዎች ለመተግበሪያዎቹ የሰጡትን ደረጃና አስተያየት በደንብ መመልከት ያስፈልጋል ይላል ማልዌርፎክስ።
ስልካችን የመንቀራፈፍ፣ የመጥፋት፣ ባትሪ የመጨረስና ሌሎች ያልተለመዱ ነገሮችን ካየንበት ምናልባት በቫይረስ ተጠቅቶ ሊሆን ስለሚችል በፍጥነት አፕዴት ማድረግና አጠራጣሪ መተግበሪያዎችን ማጥፋት እንደሚገባ አሳስቧል።
ማልዌርፎክስከፕሌይ ስቶር ውጭ መተግበሪያዎችን መጫን ይበልጥ አደገኛ መሆኑንም ገልጿል።