የባትሪ ፍጆታቸው ከፍ ያሉ መተግበሪያዎችን ማስወገድና የሃይል ፍጆታቸውን መገደብን ጨምሮ የባትሪ እድሜን የሚያረዝሙ ዘዴዎችን መተግበር ይመከራል
የስማርት ስልኮች የባትሪ እድሜ ማጠር ተጠቃሚዎች አብዝተው ከሚያነሷቸው ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው።
ባትሪዎቹ በፍጥነት ያለመሙላትና ከተሞሉ በኋላም በፍጥነት የማለቃቸው ጉዳይ ተደጋግሞ ይነሳል።
ቀጣዮቹ ሰባት ከባትሪ ጋር የተገናኙ መሰረታዊ ችግሮችም ከነሚፈቱበት ዘዴ ቀርቧል፦
1. በፍጥነት አለመሙላት
የስማርት ስልኮች ባትሪ በፍጥነት ያለመሙላት ችግር ከቻርጀር፣ ከአዳፕተር እና ከስልኮቹ የቻርጀር መቀበያ (ዩኤስቢ ፖርት) ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም ከስልካችን አቅም ጋር አብሮ የሚሄድ ፈጣን ቻርጀር በመቀየር ችግሩን ማስተካከል ይቻላል። የመንቀራፈፉ ችግር ከቻርጀሩ ጋር የተያያዘ ካልሆነም በቀጣዮቹ ዘዴዎች ሊቀረፍ ይችላል።
2. የቻርጅ መንቀራፈፍ
ከቻርጀር እና አዳፕተር ውስንነት ውጭ የስማርት ስልካችን ባትሪ ለመሙላት እጅግ የሚቆይ ከሆነ ደግሞ ሁለት የመፍትሄ ዘዴዎችን መጠቀም ይመከራል።
የመጀመሪያው ስልካችን አጥፍቶ ማብራት ነው።
ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ የሶስተኛ ወገን መተገብሪያዎች መጠቀም በጊዜያዊነት የሚያስቆመውን (ሴፍ ሞድ) መጠቀም ነው። ስልካችን ባትሪው እንዳይሞላ ምናልባትም ከስልክ አምራቹ ውጭ በራሳችን የጫናቸው መተገበሪያዎች ምክንያት ሆነው ሊሆን ይችላል ብለን ስናምን ይህን አማራጭ እንጠቀማለን። ስልካችን “ሴፍ ሞድ” ላይ ለማድረግ የማጥፊያውን (ፖወርኦፍ) ምልክት ለሰከንዶች ተጭነን መቆየትና አማራጩን ሲያመጣልን ማዘዝ ይኖርብናል።
ስልካችን አጥፍተን ካበራነው በኋላ ወይንም “ሴፍ ሞድ” ላይ ካደረግነው በኋላም የሚሞላበት ፍጥነት የተንቀራፈፈ ከሆነ ስልካችን ሙሉ በሙሉ አጥፍተን ቻርጅ ለማድረግ መሞከር ሌላኛው አማራጭ ነው ተብሏል።
3. የተሞላው ሃይል በፍጥነት ማለቅ
ብዙ ተግባራትን ስንፈጽም የባትሪ ሃይል በፍጥነት የማለቁ ነገር ተጠባቂ ቢሆንም፥ ምንም ሳናደርግ በአንድ ጊዜ ሲወርድ ግን ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ማሰብ ተገቢ ነው።
ይህንንም የባትሪ አጠቃቀማችን የሚያሳየውን መረጃ በመመልከት ማወቅ ይቻላል (Settings - Battery - Battery Usage)። ይህ አማራጭ የትኛው መተግበሪያ የባትሪያችን ሃይል በፍጥነት እየበላ ያለውን መተግበሪያ ያመላክታል። በዚህም ባትሪ የሚጨርሱትን መተግበሪያዎች በሃይል ማስቆም (Force stop) አልያም በጊዜያዊነት ጥቅም እንዳይሰጡ ማድረግ ይቻላል። የኢንተርኔት ግንኙነት ሲኖር በውስጥ ስራቸውን የሚቀጥሉ መተግበሪያዎችን መርጦ ፈቃድ በመከልከልም የባትሪያችን እድሜ መጨመር ይቻላል።
የስማርት ስልካችን የብርሃን መጠን ከሁኔታዎች ጋር የተስማማ እንዲሆን ማድረግ (Settings - Display - Adaptive brightness) ሌላኛው በባለሙያዎች የሚመከር ዘዴ ነው።
የባትሪ አጠቃቀምን የሚያስተካክለውን አማራጭ (Settings - Battery - Battery Saver - Use Battery Saver on) መጠቀምም ይመከራል።
4. ስልካችን ሳንጠቀምበት በፍጥነት ባትሪው ማለቅ
ስማርት ስልኮችን ሳንጠቀምባቸው እንዲሁ ባትሪያቸው የመውረድ ምጣኔው በስአት በአማካይ ከ0 ነጥብ 5 ፐርሰንት እስከ 1 ነጥብ 5 ፐርሰንት ነው። በአንድ ስአት ውስጥ ከ3 ፐርሰንት በላይ ከቀነሰ ግን ቀጣዮቹን መፍትሄዎች መሞከር እንደሚገባ ባለሙያዎች ያነሳሉ።
የመጀመሪያው ኔትወርክ ባገኙበት አጋጣሚ ሁሉ በውስጥ ስራቸውን የሚቀጥሉ መተግበሪያዎችን መለየትና መገደብ ነው (Settings – Apps – እያንዳንዱን መተግበሪያዎች በመጫን የተፈቀደ ያልተገደበ የባትሪ አጠቃቀምን መገደብ (አልያም መተግበሪያዎቹን Uninstall ማድረግ)
ሌላኛው ብዙም የማይመከረው አማራጭ ደግሞ ስልካችን ከኔትወርክ ግንኙነት ማቋረጥ ነው (Settings - Network & internet - Airplane mode)። ይህ አማራጭ የስልክም ሆነ የኢንተርኔት ግንኙነትን የሚያቋርጥ ሲሆን፥ ኔትወርክ ሲያገኙ ስራቸውን የሚቀጥሉ መተግበሪያዎችን ስራ በማስቆም የባትሪን እድሜ ያራዝማል ነው የተባለው።
5. የባትሪ ማበጥ
የስማርት ስልኮች ባትሪ ማበጥ ከእርጂና አልያም ለረጅም ስአት ቻርጅ ከማድረግ ሊከሰት ይችላል። ከባትሪ አምራቾች የጥንቃቄ ጉድለትም በባትሪዎቹ ውስጥ የጋዝ ክምችት ሲፈጠር ባትሪዎች ያብጣሉ።
ያበጡ ባትሪዎችን በማቀዝቀዣ ውስጥ በማስቀመጥ ለማስተንፈስና ዳግም ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራ ለውጥ ስለማያመጣ መቀየሩ ብቸኛ መፍትሄ መሆኑን ባለሚያዎች ይናገራሉ። ባትሪዎቹ ከስማርት ስልኮቹ ላይ በባለሙያ ካልተወገዱም በሰዎች ጤና ላይ የጤና ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ።
6. በከፊል መሙላት
የስማርት ስልኮችን ባትሪ እድሜ ለማርዘም ጥቅም ላይ ሊውሉ ከሚችሉ ዘዴዎች አንዱ ባትሪን በከፊል መሙላት ነው። በተለይ ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ የዋሉ ባትሪዎችን ከ40 ፐርሰንት ሳይወርዱ ከ80 ፐርሰንትም በላይ ሳይሞሉ ቻርጅ ማድረግ ይመከራል። ይህ በከፊል ቻርጅ የማድረግ ዘዴ የስማርት ስልክ ባትሪዎች ለረጅም ጊዜ ለመጠቀም ያስችላል ነው የተባለው።
7. የባትሪ ሙቀት መጨመር
አንዳንድ መተግበሪያዎች የስማርት ስልኮች ባትሪዎች ሙቀት እንዲጨምር ምክንያት ይሆናሉ። በተለይ ጌሞችን መጫወት የስማርት ስልኮችን ከመጠን ያለፈ ሙቀት ይፈጥራል። አንዳንድ ያለተጠቃሚዎች እውቅና ስልካችን ላይ የሚጫኑ መተግበሪያዎችን ማጽዳት ካልቻልም የስልካችን ባትሪ ይግላል። ይህን ችግር ለመቅረፍም የባትሪ ፍጆታቸው ከፍ ያሉ እና ከእውቅናችን ውጭ ተጭነው ያገኘናቸውን መተግበሪያዎች ማጥፋት አልያም የባትሪ ፍጆታቸውን መገደብ (Restrict) ያስፈልጋል።
ከላይ ከተዘረዘሩት ዘዴዎች ባሻገር የስልካችን ባትሪ ጤናማነት የሚያሳዩ መተግበሪያዎችን በማውረድ ብዙ የሃይል ፍጆታ ያላቸውን መተግበሪያዎች መለየትና የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደምንችልም ሜክኦፍኢት ድረገጽ ላይ የወጣው ዘገባ ያሳያል።