በአሜሪካ ቴክሳስ 19 የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ህጻናት ተገደሉ
ጆ-ባይደን ክስተቱን ለማሰብ አስከ ቅዳሜ ድረስ ሰንደቅአላማዎች ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ አዘዋል
ጥቃቱ ባለፉት አስር ዓመታት በአሜሪካ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ሁሉ የከፋ ነው ተብሏል
ራሞስ የተባለ የ18 አመት ወጣት በአሜሪካ ቴክሳስ 19 የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሕጻናት ገደለ፡፡
ህጻናቱ የተገለደሉት ሳልቫዶር ራሞስ የተባለ አንድ የ18 ዓመት ወጣት በከፈተው ድንገተኛ የተኩስ እሩምታ መሆኑን የግዛቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ቴክሳስ ግዛት፣ ዩቫልዲ ከተማ ሮብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከተገደሉት ሁለቱ አዋቂዎች ሲሆኑ የተቀሩት ህጻናት መሆናቸውም ተገልጸዋል፡፡ ጥቃቱ ባለፉት አስር ዓመታት በአሜሪካ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ሁሉ የከፋ መሆኑንም ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያመላክተው፡፡
የቴክሳስ የህዝብ ደህንነት ክፍል ሳጅን ኤሪክ ኢስታራዳ ፤ ታጣቂው ጥቃት በሚፈጽምበት ወቅት ጋሻ ለብሶ፣ ኤአር-15 ከፊል አውቶማቲክ ጠመንጃ እና ሽጉጥ ይዞ ነበር ብለዋል፡፡
ታጣቂው በህጻናቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያነሳሰው ምክንያት ግልጽ አይደለም ሲሉም አክሏል ሳጅኑ፡፡
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ በከፍተኛ የድንጋጤ መንፈስ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን፤ ጥቃት ልጆቻቸውን፣ ቤተሰባቸውን ላጡ ሀዘናቸውን ገልጿል።
አሳዛኝ ክስተቱን ለማሰብ ቅዳሜ ጀምበር እስክትጠልቅ ድረስ ባንዲራዎች በየእለቱ ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡም አዘዋል ፕሬዝዳንቱ።
ከተገደሉት ሁለት አዋቂዎች አንዷ በዚያው ትምህርት ቤት የምታስተምር መምህርት ነበረች ተብለዋል።በስፋት የስፓኒሽ አሜሪካዊያን በሚበዙበት በዚህ ትምህርት ቤት 500 ሕጻናት ተማሪዎች ይገኙበታል።
ሮብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ2ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ፤ ዕድሜያቸው ከ7 እስከ 10 ዓመት ያሉ ልጆች የሚማሩበት ነው። ሳልቫዶር ራሞስ ከዚህ በፊት የገዛ አያቱን በጥይት ተኩሶ የመታ ወጣት እንደሆነም የፖሊስ መረጃወች ይጠቁማሉ፡፡