ባይደን የአሜሪካ ጦር እንዲሰማራ ያሳለፉትን ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበሉ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ገለፁ
ውሳኔው አሜሪካ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት ያለመ ነው ተብሎለታል
የሶማሊያ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት "አሜሪካ ወትሮም ቢሆን ታማኝ አጋራችን ናት" ብሏል
ባሳለፍነው እሁድ 10ኛው የሶማሊያ ፕሬዝዳንተ በመሆን የተመረጡት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ የአሜሪካ ጦር በድጋሚ በሶማሊያ እንዲሰማራ ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን የወሰኑት ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበሉ አስታወቁ።
የአሜሪካ መንግስት፤ ሀሰን ሼክ ሞሃመድ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ የቀጠናው ስጋት የሆነውን አልሻባብ ለመምታት 600 የሚሆኑ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንደሚልክ ከአንድ ቀን በፊት ማስታወቁ አይዘነጋም።
ሶማሊያ አሁን ላይ በአልሻባብ እየተፈተነች ያላት ሀገር መሆኗ የሚታወቅ ነው። በተለይም ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሶማሊያ ምርጫ መራዘም ጋር በተያያዘ በሶማሊያ ፖሊተከኞች የነበረው ሽኩቻ ሀገሪቱ ለሰላምና ጸጽታ ጉዳዮች የምትሰጠውን ትኩረት እንዲላላ ያደረገ ሁኔታ እንደነበር በርካቶች ያነሳሉ።
እናም የአሜሪካ ውሳኔ አልሻባብን ከማዳከም አንጻር ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው ተብሎለታል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት (ቪላ ሶማሊያ) በትዊተር ገጹ ባጋራው ጽሁፍ "ለመረጋጋትና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በምናደርገው ትግል አሜሪካ ወትሮም ቢሆን ታማኝ አጋራችን ናት" ብሏል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አልሻባብ ተዳክሟል በሚል 700 የአሜሪካ ጦር አባላት ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ አልሻባብ በሶማሊያ እያደረሰ ያለው የሽብር ድርጊት እየጨመረ መጥቷል በሚል የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔን እንደሻሩ ተገልጿል።
የአሜሪካ ውሳኔ አዲስ ፕሬዝዳንት ከመረጠችው ሶማሊያ ጋር አዲስ ግንኙነት ለመመስረት ማሰቧን እንደሚያሳይም ነው የተነገረው።
ሶማሊያን ለቀጣዮቹ 5 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የተመረጡት ሀሰን ሼክ ሞሃመድ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ወዳጆች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡
አልሻባብ በሶማሊያ ዋነኛ የጸጥታ ስጋት ሲሆን፤ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት ከ19 ሺህ በላይ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጣ ጦር በሞቃዲሾ የሀገሪቱን ጦር በማገዝ ላይ ይገኛል።
አሁን ላይ ከ500 ያነሰ ቁጥር ያለው የአሜሪካ ጦር በሶማሊያ ያለ ሲሆን፤ በተመረጡ የአልሻባብ ይዞታዎች ላይ የአየር ላይ ጥቃቶችን በማድረግ ላይ እንደሆነ የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።
አልሻባብ በሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተካሂዶ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዳይካሄድ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን ቢፈጽምም ምርጫው ባሳለፍነው እሁድ መጠናቀቁ ይታወሳል።
ሶማሊያ ከአልሻባብ የሽብር ጥቃት በተጨማሪ ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ እየተፈተኑባት ይገኛሉ።