ፖለቲካ
ሰሜን ኮሪያ፤ ለአሜሪካ የኮሮና ክትባቶች የድጋፍ ጥያቄ ምላሽ ሳትሰጥ ቀረች
ባይደን አሜሪካ ለቻይና ላቀረበችው የድጋፍ ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቷንም ተናግረዋል
ፕሬዝዳንት ባይደን ለመደገፍ ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም ብለዋል
ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካን የኮሮና ክትባቶች ለመቀበል ሳትፈቅድ መቅረቷን ጆ ባይደን ተናገሩ፡፡
ጆ ባይደን ክትባቶችን ለመስጠት ብንፈልግም ፒዮንግያንግ ፈቃደኛ አይደለችም ብለዋል፡፡
የ76 ዓመቱ አዛውንት በደቡብ ኮሪያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በሴዑል ከፕሬዝዳንት ዩን ሱክ-ዪዖል ጋር በሰጡት የጋራ መግለጫም ነው ፕሬዝዳንት ባይደን ይህን የተናገሩት፡፡
"ለሰሜን ኮሪያ ብቻም አይደለም ለቻይና ጭምር ለማስጠት ጠይቀናል፤ ሆኖም ምላሽ አላገኘንም" ብለዋል ባይደን በጋዜጣዊ መግለጫቸው፡፡
ሰሜን ኮሪያ ከሰሞኑ ኦሚክሮን የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በሃገሯ መከሰቱን አስታውቃ ነበር፡፡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ብታዝም 25 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝቧ ችግር ላይ እንዳይወድቅ ተሰግቷል፡፡
የሃገሪቱ መንግስት ሚዲያዎች ዛሬ ቅዳሜ እንደዘገቡት ከሆነ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች በትኩሳትና ብርድ ብርድ መታመማቸውን ዘግበዋል፡፡ እስካሁን የ66 ሰዎች ህይወት ማለፉንም ነው የዘገቡት፡፡ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በዚህም ፒዮንግያንግ የጸረ ኮሮና ምላሽዋን ከፍ አድርጋ ጥብቅ ቁጥጥርን በማድረግ ላይ ነች፡፡