ተቃውሞውን ተከትሎ በነበሩበት የእስር ሁኔታም ላይ ታሳሪዎቹ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል
ለሳምንታት ታስረው የቆዩ የሱዳን ተቃዋሚዎች ከእስር መለቀቃቸው ተመድ አስታወቀ፡፡
የሱዳንን መፈንቅለ መንግስት በመቃወም ታስረው ከነበሩት 135 ሰዎች 115ቱ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብን ጨምሮ ጠበቆች በፈጠሩት ጫና መለቀቃቸውን ተመድ አስታውቋል፡፡
የጥቅምት 25ቱ የሱዳኑ መፈንቅለ መንግስት የ82 ሰዎች ህይወት የቀጠፈና ከ 2ሺ በላይ የሚሆኑትን ለከፍተኛ ጉዳት የዳረገ ክስተት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ በተደረገው የሹመት ድልድል በቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ጊዜ ቁልፍ ሚና የነበራቸው አካላት የሀገሪቱ የስለላ አገልግሎት በትረ ስልጣን እንዲጨብጡ መደረጉ፤ በሱዳን ከፍተኛ የተቃውሞ ድምጽ እንዲሰማ ያስገደደና በርካቶች ወደ ዘብጥያ እንዲወርዱ ያደረገ ምክንያት እንደነበርም የሚታወስ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ህንፃ ፊት ለፊት በተካሄደው ተቃውሞ አክትቪስት በመሆን ሚናውን ሲወጣ የነበረው ሻሂናዝ ጀማል ተቃውሞውን ተከትሎ ሰዎች ሲታሰሩበትና በየእስር ቤቱ ሲታጎሩበት የነበረ ሁኔታ ኢ-ፍትሃዊ እንደነበር ተናግሯል፡፡
“ምንም አይነት የተደረገ ምርምራ የለም፤ ሰዎች ካለ ምክንያት ነበር ወደ ወህኒ የሚወረወሩት” ማለቱንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳን የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፅህፈት ተወካይ የሆኑት አዳማ ዲንግ የተቀሩት ሁሉም ተቃዋሚዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።
አዳማ ዲንግ "በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የህግ የማስከበር ስልጣን ለአጠቃላይ የጸጥታ ሃይሎች መሰጠቱ እንዲሁም ለእነዚህ ሃይሎች የተሰጠው ጊዜያዊ ያለመከሰስ መብትን በተመለከተ የነበረኝን ስጋት አቅርቤ ነበር"ም ሲሉም አስታውሷል።
ከታሳሪዎቹ መካከል ሰላማዊ ሰልፈኞች፣ የአካባቢ ተቃዋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የማህበር አባላት እና ፖለቲከኞች፣ የተወሰኑት በተቃውሞ ጊዜ የታሰሩ እና ሌሎችም ከየቤታቸውና ከሌሎች አካባቢዎች የተወሰዱ መሆናቸውንም ነው የህግ ባለሙያዎች ያስታወቁት።
የአስቸኳይ ጊዜ ጠበቆችና ተሟጋች ቡድን አካል የሆኑት ጠበቃ ኢናም አቲዬ፤ ምንም እንኳን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታሰሩም እስረኞቹ ከጠበቆቻቸው፣ከዶክተሮች እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ መከልከላቸውን ትክክል አይደለም ሲሉ ነቅፏል፡፡
የሱዳን ተቃዋሚዎች ጉዳይ በሱዳናውያን ዘንዳ ዓቢይና መነጋገሪያ አጀንዳ ቢሆንም የሱዳን አቃቤ ህግ ቢሮ በጉዳይ ላይ እስካሁን ምንም ያለ ነገር የለም ተብሏል፡፡