የአፍሪካ ሀገራት የዘርማጥፋት ወንጀልን ለመከላከል የጸደቀውን የ1948ቱ ኮንቬንሽን ሊፈርሙ ይገባል- ተመድ
ሙሳ ፋኪ በሩዋንዳ ጄኖሳይድ ከተፈጸመ በኋላ “ፖል ካጋሜ ነገሮች የተቆጣጠሩበት መንገድ የሚደነቅ ነው” ሲሉ አድንቋል
በሩዋንዳ ቱትሲዎች ላይ የተፈጸመው “የዘር ማጥፋት ወንጀል 28ኛ ዓመት መታሰቢያ” በአፍሪካ ህብረት ተከብሯል
የአፍሪካ ሀገራት በ1948 የዘርማጥፋት ወንጀል ለመከላከል የጸደቀውን የ1948ቱ ኮንቬንሽን እንዲፈርሙ በተበባሩት መንግስታት የዋና ጸሀሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የዘርማጥፋት መከላከል ልዩ አማካሪ ዋይሪሙ ንደሪቱ ጠየቁ፡፡
ልዩ አማካሪዋ ይህን ያሉት፤ በዛሬው እለት “በሩዋንዳ ቱትሲዎች ላይ የተካሄደው የዘርማጥፋት ወንጀል 28ኛ ዓመት መታሰቢያ” ምክንያት በማድረግ በአፍሪካ ህብረት ባስተላለፉት መልእክት ነው፡፡
ዋይሪሙ ንደሪቱ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት ፤ ከ28 ዓመታት በፊት የሩዋንዳ ቱትሲዎች ሰብአዊነትን ዝቅ መደረጉንና በወቅቱ የሀገሪቱ መንግስት እና የኢንተርሃምዌ ሚሊሻዎች በቱትሲዎች ላይ የዘር ማጥፋት መፈጸማቸው አስታውሰዋል፡፡
የሩዋንዳው ጄኖሳይድ የሰው ልጆች ሊማሩበት የሚገባ ጥቁር ታሪክ ነው ያሉት ልዩ አመካሪዋ፤ “መቼም ቢሆን የዘር ማጥፋት ወንጀሉ ሰለባ የሆኑት ወገኖች መዘንጋት የለብንም” ብለዋል፡፡
ልዩ አማካሪዋ መሰል ድረጊት በአፍሪካ ምድርም ሆነ በዓለም እንዳይደገም የአፍሪካ ሀገራት ሀገራት እንደፈረንጆቹ 1948 የተደረሰው የወንጀል መከላከልና የዘር ማጥፋት ቅጣት ኮንቬንሽን እንዲፈርሙ ሲሉም ጠይቋል፡፡
የዛሬ 28 ዓመት ሚያዝያ 7/1994 ከቀኑ 6፡00 የጀመረውና ለ100 ቀናት ያክል በሩዋንዳ ምድር የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አንድ ሚልዮን ገደማ ሰዎች የተገደሉበት እንደነበር ይታወቃል፡፡
እንደ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ከሆነ፤ በሩዋንዳ የሆነው ነገር የሰው ልጆች ሊማሩበት የሚገባ አሳዛኝ የታሪክ ክስተት ነው፡፡
ሊቀ መንበሩ፤ሩዋንዳውያን ከ28 ኣመታት በኋላ ይቅር ተባብለው ፤ ግን የተፈጠረውን ጥቁር ጠባሳ ሳይረሱ በእርቅ ለውጥ ወደ ማምጣት መሸጋገራቸውም እንዲሁ ዓለም ሊማርበት የሚገባ ነው ብለዋል፡፡
“የሩዋንዳ መሪዎች በተለይም ደግሞ ፖል ካጋሜ ነገሮች የተቆጣጠሩበት መንገድ የሚደነቅ ነው” ሲሉም ለሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ያላቸውን አድናቆት ገልጿል፡፡
በቅኝ አገዛዙ ዘመን የተፈጠሩ ጎሳን መሰረት ያደረጉ አስተሳሰቦች፤ ሩዋንዳውያን ከነጻነት በኋላ ለገጠማቸው የፖለቲካ ውድቀት ምክንያቶች እንደነበሩ የገለጹት ሊቀ መንበሩ፤ “በቱትሲዎች ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ድርጊት መነሻው ይህ (ጎሳን መሰረት ያደረገ አስተሳሰብ) ነበር” ሲሉም ተናግሯል፡፡
በኢትዮጵያ የሩዋንዳ አምባሳደር ሆፕ ቱምኩንዴ ጋሳቱራ በበኩላቸው ፡ የሩዋንዳ ጄኖሳይድ በሚልዮን የመቆጠሩ የምንወዳቸው ቤተሰቦቻችን ያጣንበት ነበር ሲሉ የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታ አስታውሷል፡፡
አምባሳደሯ የነበረው ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ ነገሮች ወደ መጥፎ ሁኔታ ሳያመሩ መቆጣጠር ሲቻል “ወቅቱ ሩዋንዳ ከዓለም የተገለለችበት፤ ዓለም በሩዋንዳ ምድር የሰው ልጅ ህይወት እየረገፈ ጥጉን ይዞ ሲመለከት የነበረበት መሆኑ ነው” ሲሉም አክሏል፡፡
ይህ በዚህ ዘመን አንዲደገም መፍቀድ የለብንምም ብለዋል ፡
አምባሳደሩ መሰል አሳዛኝ ክሰተቶች እንዳይገሙ መጪው ትውልድ በመልካም እሴቶች በመገንባት ረገድ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡አፍሪካ ህብረት የዛሬ 28 ዓመት በሩዋንዳ የተፈጸመውና የዘር ማጥፋት ወንጀል መታሰቢያ መድረክ በየዓመቱ እንደሚያዘጋጅ ይታወቃል፡፡
የዚህ ዓመት መሪ ቃል “አስታውስ-ተባበር-ቃልህን አድስ” የሚል ሲሆን፤ በርካታ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የተመድ ኤጄንሲዎች ተወካዮች በተገኙበት ታስቦ ውሏል፡፡