“ሱዳን ከሽብርተኝነት ዝርዝር መውጣቷ በሀገሪቱ መረጋጋትን ያጠናክራል” ዩኤኢ
ሱዳን ከአሜሪካ ሽብርተኝነትን የሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ዛሬ በይፋ ተሰርዛለች
አሜሪካ ሱዳንን በተመለከተ የወሰደችውን እርምጃ ዩኤኢ አድንቃለች
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አሜሪካ ሱዳንን ሽብርተኝነት ከሚደግፉ ሀገሮች ዝርዝር ውስጥ ማስወጣቷን አድንቃለች፡፡
የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ሱዳን ለዓመታት ከቆየችበት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገለልተኝነት በመውጣቷ ለሀገሪቱ መንግስት እና ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፏል፡፡
ሚኒስቴሩ ያወጣው መግለጫ አክሎም ይህ እርምጃ ለሱዳን ፀጥታ ፣ መረጋጋት እና ብልጽግና ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው ብሏል፡፡
ሱዳን ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ መሰረዟ ከዛሬ ታህሳስ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን በካርቱም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቀደም ሲል አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ሱዳን ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ መሰረዟ ከዛሬ ጀምሮ በፌዴራል መዝገብ እንዲታተም መፈራረማቸውንም ኤምባሲው ገልጿል፡፡ ሱዳን ከዝርዝሩ መሰረዟን የአሜሪካ ኮንግረስም ይፋ አድርጓል፡፡
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በትዊተር ገጻቸው “ዛሬ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በኋላ የምንወዳት ሀገራችን ስም ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ መውጣቷ ለህዝባችን ታውጇል ብለዋል፡፡ ዛሬ ሁሉንም ታሪካችንን ፣ የሕዝባችንን ሥልጣኔ ፣ የአገራችንን ታላቅነት እና የአብዮታችንን ንቃት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የምናሳይበት ነው” ሲሉም ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት ሊቀመንበር ሌ/ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃንም እንዲሁ ለህዝባቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡