በምስራቅ ኢትዮጵያ 2.1 ሚሊየን ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል- ተመድ
በድርቅ ምክንያት ለችግር ለተዳረጉ ዜጎች ለመድረስም 65 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ያስፈልጋል
ባህላዊ የውሃ ምንጮች መድረቅና የጉድጓድ ውሃ አቅርቦት ውስንነት ክፍተኛ ችግር እያስከተለ ነው
በምስራቅ የኢትዮጵያ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልገቸው በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (ዩ.ኤን.ኦቻ) አስታወቀ።
ማስተባበሪያው በትናንትናው እለት ባወጣው ሳምንታዊ መግለጨው በምስራቅ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚኖሩ ወደ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ገደማ የሚጠጉ ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ማለቱን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ባህላዊ የውሃ ምንጮች መድረቅ እንዲሁም ከጉድጓድ ውሃ የሚወጡ የውሃ አቅርቦቶች ውስንነት ክፍተኛ ችግር እያስከተለ መሆኑን በመግለጽ፤ በክልሉ በአፋጣኝ የዉሃ ማጓጓዣ ተሸከርካሪዎች አቅርቦት እንደሚያስፈልግም አስታውቋል።
በክልሉ በድርቅ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወደ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ገደማ የሚጠጉ ሰዎች የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ አስቸኳይ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉም ተመድ ገልጿል።
በክልሉ በድርቅ ምክንያት ለችግር ለተዳረጉ ዜጎች ለመድረስም 65 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልገውም የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ አስታውቋል።
ግጭቶች፣ ድርቅ እና በየወቅቱ የሚደርሱ የጎርፍ አደጋዎች የሶማሌ ክልልን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የተለያዩ ሰብዓዊ ቀውሶችን ሲያስከትል መቆየቱንና የሰብአዊ ድጋፍ የሚስፈልጋቸው ሰዎች እንዲያሻቅብ ማድረጉን ድርጅቱ አስታውሷል።
ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት ሰብዓዊ ድጋፍ የሚስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት መሆኑንም አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ በተያዙ ሰዎች ብዛት ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን፤ ከአፍሪካ ደግሞ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።