ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፎች የሚሆን ከፍተኛ የገንዘብ እጦት ገጥሟታል
በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከ15 ሚሊዬን ለሚልቁ ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍን ለማድረስ ታቅዷል
930 ሚሊዬን ዶላር ገደማ የገንዘብ ድጋፍን በአስቸኳይ ትፈልጋለችም ተብሏል
በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከ15 ሚሊዬን ለሚልቁ ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍን ለማድረስ ታቅዷል
ኢትዮጵያ እስከተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት አጋማሽ ድረስ በሰብዓዊ ምላሾች ረገድ የነበራትን አፈጻጸም የሚያሳየው የግምገማ ውጤት ይፋ ሆነ፡፡
የግምገማ ውጤቱ ይፋ የሆነው በኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመነ ዳሮታ እና በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ እና የሰብዓዊ ድጋፎች አስተባባሪ ካትሪን ሶዚ(ዶ/ር) ነው፡፡
በተያዘው ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ለ15 ነጥብ 2 ሚሊዬን ሰዎች ምግብ እና ምግብ ነክ የሆኑ ሌሎችንም ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ ድጋፎች ለማድረግ መታሰቡን የሚያትተው ዕቅዱ ለማስፈጸሚያ የሚሆን 1 ነጥብ 4 ቢሊዬን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልጋል ይላል፡፡
ግምገማው በዋናነት በበልግ ዝናብ የምርትና ምርታማነት ተጽዕኖ ላይ ትኩረት አድርጎ የተካሄደ ሲሆን በአርብቶ አደርና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ከውሃና ግጦሽ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችንም ዳስሷል፡፡
ከአንበጣ መንጋ፣ከጎርፍ፣ከጸጥታና ደህንነት እንዲሁም ኮሌራን ከመሳሰሉ ወረርሽኞች ጋር በተያያዘ የገጠሙ ሰብዓዊ ችግሮችም ተገምግመዋል፡፡
ዓለምን ባስጨነቀው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳይስተጓጎሉ ሰብዓዊ ድጋፎቹን ማድረስ ይገባልም ነው የተባለው በዕቅድ ግምገማ መድረኩ፡፡
መንግስት ተቀዳሚ ትኩረቱ ወረርሽኙ ቢሆንም ድጋፎቹን ከማድረግ እንዳላስተጓጎለውም አቶ ዳመነ ተናግረዋል፡፡
ባሳለፍነው ወርሃ ሃምሌ የተደረጉ የፋይናንስ ድጋፍ ትንተናዎች አሁንም ያልተሟሉ የድጋፍ ፍላጎቶች እንዳሉ አመልክተዋል፡፡
በዋናነት ምግብ ነክ ከሆኑ ፍላጎቶች ውጭ የሚደረገው ድጋፍ እ.ኤ.አ ከ2012 ወዲህ እጅግ አሽቆልቁሏል ተብሏል፡፡
ለምግብ ነክ ፍላጎቶች ሲደረግ የነበረው ድጋፍም ቢሆን አሽቆልቁሏል፡፡ በተለይ ሃምሌ ላይ የነበረው ድጋፍ ባለፉት 5 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ አሽቆልቁሏል እንደ ትንተናዎቹ ገለጻ፡፡
አስቸኳይ ድጋፎች የማይደረጉም ከሆነ ጉዳቶቹ ይበልጥ ተባብሰው ሴቶችን፣ህጻናትን፣ አዛውንቶችን እና አካል ጉዳቶችን ከዚህም በበለጠ ሊያጋልጥ ይችላል፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የዓለም አቀፍ አጋሮችን አስቸኳይ ድጋፍ ይሻሉ ያሉት ካትሪን ሶዚ (ዶ/ር) አስቸኳይ ድጋፉ ወረርሽኝ ወለድ የሆኑ ችግሮች ለመቆጣጠር ብቻም ሳይሆን ቀድሞም የከፉ በነበሩ ሰብዓዊ ሁኔታዎች ላይ ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ተራዛሚ ችግሮች ጭምር ምላሽ ለመስጠት የሚያስፈልግ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወዳጅና አጋር የሆኑ ሃገራት ሰብዓዊ ስቃዮችንና ሞትን ለማስቀረት የሚያስችሉ ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፎችን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት 83 ነጥብ 1 ሚሊዬን የአሜሪካን ዶላር ቢመድብም እና 425 ነጥብ 1 ሚሊዬን የአሜሪካን ዶላር ከእርጥባን ቢገኝም አሁንም ለእቅዱ ማስፈጸሚያነት የተያዘውን 1 ነጥብ 4 ቢሊዬን የአሜሪካን ዶላር የበጀት አቅድ ለማሳካት እንዳልተቻለም ነው በግምገማ መድረኩ የተገለጸው፡፡
929 ነጥብ 6 ሚሊዬን የአሜሪካን ዶላር ጉድለት አለውም ተብሏል፡፡