የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለትግራይ ሰብዓዊ ድጋፎች የሚውል 170 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አስታወቀ
በትግራይ 4.5 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል መባሉ የሚታወስ ነው
ፕሮግራሙ በክልሉ ለ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጿል
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ለሚያከናውነው የሰብዓዊ መብት ድጋፍ 170 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አስታወቀ።
በክልሉ በተካሄደው ውጊያ ምክንያት ዜጎች ለከፋ ሰብአዊ መብት ጥሰት ተዳርገዋል ያለው ፕሮግራሙ ለተጎጂዎች ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጿል።
ድርጅቱ በድረገጹ ባወጣው መግለጫ በክልሉ ለተፈናቀሉ እና ለምግብ እጥረት ለተዳረጉ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ 170 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል።
በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም የምግብ ድርጅት ከነዚህ ውስጥ ለ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች እየደገፈ መሆኑን አስታውቋል።
በክልሉ የተካሄደው ውጊያ የሰብል ስብሰባ በሚካሄድበት ወቅት መሆኑ የተጎጂ ዜጎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል የሚለው ድርጅቱ ገበያዎች፣ሰብሎች እና ሌሎች መሰረታዊ መገልገያዎች ከጥቅም ዉጪ መሆናቸውን አስቀምጧል።
የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ስቴቨን ኦማሞ በትግራይ ማዕከላዊ እና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞኖችን እንደጎበኙ ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ መንግስት ህይወት አድን እርዳታዎችን ለተጎጂዎች በማድረስ ላይ ይገኛል። ይሁንና የሀብት እጥረት ስላለ ተጨማሪ የረድኤት ድርጅቶች ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ ላሉ ለ875 ሺህ ነፍሰጡሮች፣ አጥቢ እናቶች እና ህጻናት በቀጣዮቹ ስድስት ወራት አልሚ ምግቦችን መስጠቱን እንደሚቀጥልም ገልጿል።
ተቋሙ ከዚህ በተጨማሪም ከ35 ሺህ በላይ ለሚሆኑ በክልሉ ለሚገኙ አዲ ሀሩሽ እና ማይ አይኒ የስደተኛ ጣቢያ ለሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።