ልዩልዩ
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለትግራይ ክልል የሚውል 46 ቶን የሰብዓዊ ዕርዳታ አደረገች
ዩኤኢ ሱዳን ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች የሚውል 18.3 ሚሊዮን ድርሃም ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች
ዩኤኢ ለኢትዮጵያ ህዝብ የምታደርገው ድጋፍ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የሚገኙት የሀገሪቱ አምባሳደር ገልጸዋል
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 46 ቶን የምግብ እና የጤና አቅርቦቶችን የያዘ የእርዳታ አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ ልካለች፡፡
ዕርዳታው በትግራይ ክልል ያለውን የሰብዓዊ ችግር ለመቅረፍ የሚደረገው የድጋፍ ማዕቀፍ አካል ነው፡፡ ዕርዳታው ዛሬ መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ቦሌ አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር መሐመድ ሳሌም “የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት” መሆኑን ጠቅሰው ፣ ይህ ድጋፍም “ወንድም ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ” በዩኤኢ መንግስት የተለገሰ መሆኑን እና ቀጣይነት እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ አክለውም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የላከችው ድጋፍ “በትግራይ ክልል በጦርነት እና በኮቪድ -19 ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚውል ነው” ብለዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ለተፈናቀሉ ወገኖች 18.3 ሚሊዮን ድርሃም (5 ሚሊዮን ዶላር) ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷም የሚታወስ ነው፡፡