የቻይናውን የቪዲዮ መተግበሪያ ቲክ ቶክን ያገዱ የአሜሪካ ግዛቶች 20 ደረሱ
80 ሚሊዮን የሚያህሉ አሜሪካውያን ቲክ ቶክን እንደሚጠቀሙ መረጃዎች ይጠቁማሉ
ግዛቶቹ የቪዲዮ መተግበሪያው(ቲክ ቶክ)ን ያገዱት “የደህንነት ስጋት ነው” በሚል ነው
የቻይና ቪዲዮ መተግበሪያ የሆነውን ቲክ ቶክን ያገዱ የአሜሪካ ግዛቶች 20 ደረሱ፡፡
ግዛቶቹ ቲክ ቶክን ያገዱት ከኤሌክትሮኒክስ ደህንነት ጋር በተያያዙ ስጋቶች ምክንያት ሲሆን ከአሁን በኋላ በመንግስትን ኮምፒውተሮች ጥቅም ላይ እንይውል ከልክለዋል፡
ኬንታኪ በቅርቡ በቲክ ቶክ ላይ እገዳውን ከጣሉ ተጨማሪ የአሜሪካ ግዛቶች ሆናለች፡፡
የኬንታኪ ግዛት የመንግስት ሰራተኞቹ በቻይና ባለቤትነት የተያዘውን የቪዲዮ መተግበሪያ (ቲክ ቶክ) “ለህግ ማስፈጸሚያ ዓላማዎች ካልሆነ በስተቀር” በመንግስት የሚተዳደሩ መሳሪያዎችን እንዳይጠቀሙ መከልከሉ አስታውቋል፡፡
የዊስኮንሲን እና የሰሜን ካሮላይና ገዥዎችም በተመሳሳይ ቲክ ቶክን ከመንግስት ኤጀንሲዎች የሚከለክሉ ትዕዛዞችን ሐሙስ እለት ፈርመዋል።
ኦሃዮ ፣ ኒው ጀርሲ እና አርካንሳስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ተመሳሳይ እርምጃዎችን የወሰዱ ግዛቶች ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኒው ጀርሲ እና ዊስኮንሲን የሁዋዌ ቴክኖሎጂስ ኢንክ፣ሂክቪዥን ኢንክ፣ የዊቻት ባለቤት ቴንሰንት ሆልዲንግስ ኢንክ እና ዜድቲኢ ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ከሌሎች የቻይና ኩባንያዎች ሻጮችን፣ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን በማገድ ከፍተኛ ርቀት መሄድ ችለዋል፡፡
የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ራይ በህዳር ወር ላይ የቪዲዮ መተግበሪያው የብሄራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ ይጥላል ብለው ከተናገሩ በኋላ ቲክ ቶክን ከአሜሪካ መንግስት ኤጀንሲዎች ለማገድ የሚደረጉት ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
ሬይ በወቅቱ ሲናገሩ የቻይና መንግስት በተጠቃሚዎች ላይ ተጽእኖ ለማድረግ ወይም መሳሪያዎቻቸውን ለመቆጣጠር መተግበሪያውን ሊጠቀምበት ይችላል የሚለውን ስጋት ጠቁመው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ወር የፌደራል ሰራተኞች ቲክ ቶክን በመንግስት በተያዙ መሳሪያዎች ላይ እንዳይጠቀሙ መከልከልን የሚያካትት የመንግስት የገንዘብ ድጋፍ ህግን አጽድቀዋል።
የአሜሪካ ኮንግረስም በጸጥታ ስጋት ምክንያት ቲክ ቶክን ከአባላቱ እና ከሰራተኞቹ መሳሪያዎች አግዷል።
መሰረቱን ቤጂንግ ያደረገው ተቋሙ (ቲክ ቶክ) ግን በአሜሪካ እና በሌሎች ሀገራት የሚቀርበው ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው ሲል ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡
በአሜሪካ ብቻ ከ80 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክ ቶክ የአሜሪካ ዜጎችን የግል መረጃ ማግኘት እንደማይቻል እና ይዘቱ በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲም ሆነ በቤጂንግ ቁጥጥር ስር ያለ ማንኛውም አካል ሊጠቀምበት እንደማይችል ለዋሽንግተን ለማረጋገጥ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነም አስታውቋል፡፡