ኩባንያው አሁን ላይ በመላው ዓለም የሚገኙ 1 ቢሊዮን ደንበኞች እንዳሉት ተገልጿል
ቲክ ቶክ በኦንላይን ኢንተርኔት በመጎብኘት ጎግልን በመብለጥ የዓለማችን ቀዳሚ ገጽ ሆነ ተባለ፡፡
የቻይናው ቲክቶክ ኩባንያ እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆቹ 2021 ዓመት የአሜሪካውን ጎግል በመብለጥ በደንበኞች ተመራጭ መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ቲክቶክ አጫጭር እና አዝናኝ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከሚጋሩባቸው የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ተመራጩ መሆን ችሏል፡፡ቲክቶክ በተለይም ካሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ በዓለማችን ተወዳጅ የትስስር ገጽ ሆኗል ተብሏል፡፡
ኩባንያው በተለይም ካሳለፍነው ነሀሴ ወር ጀምሮም ላለፉት ዓመታት በበይነ መረብ አሳሾች ብዛት ዓለምን ተቆጣጥሮት የነበረው የአሜሪካው ጎግል ኩባንያን እንደበለጠ የሩሲያው አርቲ ዘግቧል፡፡
ቲክ ቶክ ከአምስት ዓመት በፊት በፈረንጆቹ በ2016 ዓመት የተመሰረተ ሲሆን አሁን ላይ በመላው ዓለማችን የሚገኙ 1 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት፡፡
አሁን ላይ 140 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ እንዳለው የሚጠቀሰው ቲክቶክ ኩባንያ የኮሮና ቫይረስ መከሰት ተጨማሪ ደንበኞች እና ገቢ እንዲያገኝ እገዛ አድርገውለታል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቲክቶክ ኩባንያ እድገት አስፈሪ መሆኑን ተከትሎ አሜሪካዊያን ቲክቶክ ኩባንያን እንዲገዙት ግፊት ሲያደርጉ ነበር፡፡