ቲክ ቶክ በሩሲያ የቀጥታ ስርጭት እና አዳዲስ ቪዲዮ የመጫን አገልግሎቱን አገደ
ሩሲያ 15 አመታት የሚያስቀጣ የሚዲያ ህግ ወጥቷል
ቲክ ቶክ ርምጃውን የወሰደው ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ሩሲያ ያወጣቸውን አዲስ የሚዲያ ህግ እንደምታ በማየት ነው ብሏል
የቻይና እንደሆነ የሚነገርለት የቪድዮ መተግበሪያ ቲክ ቶክ በሩሲያ የሚያስተላለፈው የቀጥታ ስርጭትም ሆነ አዳዲስ ፋይሎች መጫን ማገዱን አስታወቀ፡፡
ቲክ ቶክ ለማቆም የተገደደው ከወቅታዊ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተፈረመውን አዲስ የሚዲያ ህግ እንደምታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑንም በምክንያትነት አስቀምጧል፡፡
ቲክ ቶክ በትዊተር ገጹ ላይ አንዳጋራው ከሆነ "የዚህን ህግ የደህንነት አንድምታ በምንገመግምበት ጊዜ የቀጥታ ስርጭትን እና አዲስ ይዘቶችን ያሏቸው ቪዲዮዎቸን አገልግሎታችን ከማገድ ሌላ አማራጭ የለንም" ብለዋል፡፡
ውሳኔው በመልእክት መለዋወጥ አገልግሎቱ (ኢን-አፕ ሜሴጂንግ) ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ የለም ሲልም አክሏል ኩባንያው፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ላይ ከያዘችው አቋም ተቃራኒ የሆነ መረጃ ማሰራጨት እስከ 15 አመት እስር እንዲያስቀጣ ሆኖ በፕሬዝዳንት ፑቲን ፊርማ ጸድቋል፡፡
በምእራባውያን የምትደገፈው ዩክሬን፣ ምእራባውያን በዩክሬን ከበረራ ነጻ ቀጣና እንዲያውጁ ብትጠይቅም፤ ምእራባውያን ርምጃው ቢወሰድ ከሩሲያ ጋር በቀጥታ ስለሚያጋጭ አናውጅም ብለዋል፡፡
የምእራባውያን ወታደራዊ ጥምረት በሆነው የኔቶ ድክመት ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ ሲሉ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በትናንትናው እለት ተናግረዋል፡፡
ምእራባውያን ይህን ባለማድረጋቸው ዩክሬን ብቻዋን እየዋጋች ነው ሲሉ ዘለንስኪ ተደምጠዋል፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ “በዩክሬን የተጀመረው ወታደራዊ ተልዕኮ” ሀገራቸው ባቀደችው መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ ጦር እስካሁን ባካሄደው “ዘመቻ” በደቡብ ዩክሬን የምትገኝው ኬርሶን ከተማ ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችንና ከተሞችን መቆጣጠር ችሏል፡፡ የሩሲያ ወታራዊ ዘመቻ በምዕራባውያን ዘንድ ያልተወደደ በመሆኑ በርካታ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ጎርፍ እየወረደባት ነው፡፡ ምዕራባውያን የኢኮኖሚ ማእቀብ ከመጣል በተጨማሪ የአየር ክልላቸውን ለሩሲያ ዝግ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተችው፣የኔቶ ጦር ዩክሬንን ጨምሮ ወደ ቀድሞ የሶቬት ህብረት ሀገራት እተሰፋፋ ነው፤ይህም ለደህንነቷ አስጊ እንደሚሆን በመግለጽ ነበር።የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እደቀጠለ ቢሆንም ሀገራቱ ችግሩን ለመፍታት ሁለተኛ ውይይታቸውን ጀምረዋል።