ከኢስታንቡል ከንቲባነት እስከ ቱርክ ፕሬዝዳንትነት የዘለቀው የኤርዶሃን የፖለቲካ ህይወት ምን ይመስላል?
በፈረንጆቹ 1954 የካቲት ወር ላይ በጉንይሱ ከተማ የተወለዱት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በ13 አመታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ኢስታንቡል አምርተዋል።
በታዳጊ እድሜያቸውም ሎሚ እና ሰሊጥ የተቀባ ዳቦ በመሸጥ ቤተሰባቸውን ይደግፉ ነበር።
በማርማራ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከመቀበላቸው አስቀድሞም የእስልምና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
በ1970 እና 80ዎቹ ወደ ፖለቲካው አለም የተቀላቀሉት ኤርዶሃን ዌልፌር የተሰኘውን ፓርቲ ተቀላቅለው በ1994 የኢስታንቡል ከንቲባ ሆነው ተመርጠዋል።
ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ግጥም በማቅረባቸው ለአራት ወራት ለእስር ሲዳረጉም ከፖለቲካው ገለል ለማለት ቢገደዱም በፈረኖቹ 2001 አብዱላህ ጉል ጋር በመሆን ጀስቲስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ፓርቲን (ኤኬፒ) በማቋቋም ተመልሰዋል።
ፓርቲያቸው በ2002 በተካሄደው ምርጫ አብላጫውን ድምጽ አግኝቶም በ2003 የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ቲአርቲ ወርልድ አውስቷል።
ላለፉት ሁለት አስርት አመታትም ከዘመናዊቷ ቱርክ መስራች ከማል አታቱርክ በመቀጠል ወሳኙ መሪ ሆነው ሀገሪቱን እየመሩ ነው።