የኤርዶሃን መመረጥ ለሃያላኑ ሀገራት አንድምታው ምንድን ነው?
የአሜሪካ እና ሩሲያ ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የሀገራትና አለማቀፍ ተቋማት መሪዎች ለኤርዶሃን የደስታ መልዕክት እያስተላለፉ ነው
የእስያ እና አውሮፓ ድልድይ የሆነችውን ቱርክ ለሁለት አስርት የመሩት ኤርዶሃን ትናንት በተካሄደው የዳግም ምርጫ አሸናፊ ሆነዋል
የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ከመላው አለም የደስታ መግለጫ እየደረሳቸው ነው።
የአሜሪካ እና ሩሲያ ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የሀገራት መሪዎች ኤርዶሃን ትናንት በተካሄደው ምርጫ ስላሸነፉ ደስታቸውን ገልጸውላቸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አለማችንን የተጋረጡባትን የጋራ ችግሮች ለመፍታት ከኤርዶሃን ጋር በትብብር እንሰራለን ብለዋል። ሀገራቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ሰጣ ገባ ባያጣውም ባይደን የኔቶ እና የሁለትዮሽ ትብብራችን እንደሚያድግ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው የምርጫው ውጤት አሳማኝ እና የኤርዶሃን ጠንካራ የስራ ትጋት ማሳያ ነው ብለውታል።
የቱርክ ህዝብ የሀገራቸውን ሉአላዊነት እንዲጠበቅና የአንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ከየትኛውም ሃይል ገለልተኛና ተጽዕኖ የማይደርስበት እንዲሆን ፍላጎታቸውን ያስረገጡበት መሆኑንም አክለዋል።
ኤርዶሃን ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ከጀርመኑ መራሂ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ፣ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኡርሱላ ቮን ደር ላይን እና ከኔቶ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግም የደስታ መልዕክት ተላልፎላቸዋል።
የኤርዶሃን ዳግም መመረጥን ተከትሎ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሃፊው የደስታ መግለጫን ቢያወጡም ስጋት ግን አላቸው። በተለይ ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል የጀመረችውን ጥረት ወደኋላ እንዳይጎትቱት በሚል።
የንስ ስቶልተንበርግ ግን በሃምሌ ወር በቱርክ የሚካሄደው የኔቶ ጉባኤ የተቃና እንዲሆን ከኤርዶሃን ጋር ለመስራት ፍላጎታቸውን በመግለጽ የስቶኮልምን ጉዳይ በይደር አቆይተውታል።
የአውሮፓ እና የእስያ ድልድይ ናት የምትባለው ቱርክ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የኤርዶሃን መሪነት ጸረ አውሮፓዊ አቋም እያንጸባረቀች ወግ አጥባቂ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እየተስፋፉባት መሆኑን ምዕራባውያኑ ሲያነሱ ይደመጣል።
በተለይ ከሩሲያ ጋር ወዳጅነቷን ስታጠብቅ ይሄው ወቀሳ ጎላ ብሎ መደመጥ ጀምሯል።
ቱርክ በፈረንጆቹ 2017 ከሩሲያ ኤስ 400 ጸረ ሚሳኤሎችን ከሩሲያ እንደምትገዛ ማሳወቋ የኔቶ አባል ሀገራትን ክፉኛ አስቆጥቶ፥ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም በአንካራ ላይ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል።
ሩሲያ እና ቱርክ በሶሪያ በተቃርኖ ቢሰለፉም ጠንካራ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ትብብርን መመስረት ችለዋል።
አንካራ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሲጀመር ከኔቶ አጋሮቿ ጋር እንድትሰለፍ ቢጠበቅም ሞስኮን ማውገዝ እንኳን አልፈቀደችም።
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ሀገራቱን ለማደራደር ጥያቄ ከማቅረብና የጥቁር ባህር የእህል ሽያጭ ስምምነት እንዲደረስ ጥረት ከማድረግ ውጪ ምዕራባውያኑ የፈለጉትን አላደረጉም።
አሜሪካም በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ያልጣሉትን ኤርዶሃን ማቅረብ እንጂ መግፋት ይበልጥ ከፑቲን ጋር ወዳጅነታቸውን ያሰፋል በሚል በዝምታ አልፋዋለች።
ለቀጣዮቹ አምስት አመታት ቱርክን ለመምራት የተመረጡት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ፥ ከሳኡዲ አረቢያ፣ ሶሪያ፣ ግብጽ እና አርመኒያ ጋር ግንኙነታቸውን ለማደስ ቃል ገብተዋል።
የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲም ለኤርዶሃን የደስታ መልዕክት ከላኩት መሪዎች መካከል ይገኙበታል።
ኤርዶሃን በአዲሱ የስልጣን ዘመናቸው ከኒውደልሂ ጋር ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት እንደሚያድሱ ይጠበቃል። በካሽሚር ጉዳይ ከፓኪስታን ጎን ተሰልፋ የቆየችው አንካራ አሰላለፏን ልትቀይር እንደምትችል ነው ኢንዲያን ታይምስ ያስነበበው።
ምዕራባውያን ሀገራትን በመንቀፍ የሚታወቁት የ69 አመቱ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት፣ በኩርድ ታጣቂዎች፣ በአውሮፓ ህብረት እና ኔቶ ጉዳይ አቋማቸውን ይቀጥሉበታል ወይስ ያስተካክላሉ?
ከሩሲያ እና ቻይና ጋር የመሰረቱት ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትስ እስከምን ድረስ ይቀጥላል?
በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸው ቢቀጥልም ቱርክን በአለም አቀፍ መድረክ ተገዳዳሪ ያደረጉት መሪ በድምሩ ለሩብ ክፍለዘመን ስልጣን ላይ የሚያቆያቸው ድምጽ በህዝባቸው ተሰጥቷቸዋል።