በቱርክ የደመወዝ ጭማሪ ዝቅተኛ ደመወዝ ወለል 5 ቪህ የቱርክ ሊሬ ወይም 768 ዶላር ሆኗል
የቱርክ መንግስት ለሀገሪቱ የመንግስት ሰራተኞች የ45 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ማደረጉን ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኸን አስታወቁ።
ፕሬዝዳንት ኤርዶኸን የደመወዝ ጭማሪውን ይፋ ያደረጉት በሀገሪቱ የሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ 5 ቀናት ሲቀሩት እንደሆነም ተነግሯል።
ከቱርክ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ደቀም ብሎ በተካሄደ የህዝብ አስተያየት የማሰባሰብ ስራ ፕሬዝዳንት ኤርዶኸን ከተቃዋሚ እጩ ከማል ክሊግሩ በጠባብ ልዩነት እየተፎካከሩ ይገኛሉ።
- ኘሬዝደንት ኤርዶጋን ተቃዋሚዎቻቸውን "የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት" ደጋፊ ናቸው ሲሉ ከሰሱ
- ለፕሬዝዳንት ኤርዶሀን በቱርክ ታሪክ ከፍተኛ ህዝብ የታደመው የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ
ፕሬዝዳንት ኤርዶኸን የደመወዝ ጭማሪውን ይፋ ያደረጉት በዛሬው እለት በአንካራ የመንግስት ሰራተኞች ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መብቶች ዙሪያ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ነው።
በዚህ ወቅትም ፕሬዝዳንቱ፤ “የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ላይ የ45 በመቶ ጭማሪ አድርገናል፤ በዚህም ዝቅተኛውን የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ወደ 5 ሺህ የቱርክ ሊሬ ወይም 768 የአሜሪካ ዶላር ከፍ አድርገናል” ብለዋል።
ኤርዶኸን አክለውም “የሲቪል ሰርቫንቱ ጡረታ እና የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችም ከፍ ለማድረግ እየሰራን ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
በቱርክ የዋጋ ግሽበት ባሳለፍነው ዓመት ላይ 85.5 በመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ የፊታችን እሁድ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የኢኮኖሚ ጉዳይ ዋነኛው የመከራከሪያ አጀንዳ ነበር።
ቱርክን ለ20 ዓመታት የመሩት ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኸን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።
የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን እና የሀገሪቱን የዋጋ ግሽበት ወደ አንድ ዲጅት ለመውረድም ቃል ገብተዋል።