ጉዳዩን እንዲያጠኑ የተላኩ ሌሎች ሰዎችም የህመም ስሜት ማሳየታቸው ነው የተገለጸው
በሰሜናዊ አልጀሪያ ባለ አንድ ባህር ላይ የዋኙ 200 ሰዎች ታመው ሆስፒታል መግባታቸው ተገለጸ።
ሲጂቲኤን አፍሪካ እንደዘገበው ባሳለፍነው እሁድ ቴነስ በተሰኘችው ሰሜናዊ አልጀሪያ በሚገኝ ባህር ላይ ነበር 200 የአካባቢው ነዋሪዎች ዋና የዋኙት።
እነዚህ ሰዎች መታመማቸውን ተከትሎ የአልጀሪያ መንግስት በአካባቢው ያሉትን ሶስት የጨዋማ ውሃ ማጣሪያ የባህር ዳርቻዎችን ዘግቷል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም በተፈጠረው ክስተት ግራ መጋባት ውስጥ መሆናቸው ዘገባው አክሏል።
በአካባቢው ያሉ የጤና ባለሙያዎች ደግሞ ችግሩ የተከሰተው የባህሩ ውሃ በጋዝ ስለተበከለ እና ወቅቱ ነፋሻማ መሆኑ ብክለቱን ስላባባሰው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል።
የአካባቢው አስተዳድር በበኩሉ በባህሩ ላይ እቃዎችን በሚያጓጉዙበት ወቅት የተፈጠረ የውሃ መበከል ሊሆን ይችላል ሲሉ ነዋሪዎች ደግሞ በባህሩ ላይ መርዛማ አልጌ ስለተፈጠረ ይሆናል የሚሉ ግምቶችን በማስቀመጥ ላይ ናቸው።
እነዚህ ዋናተኞች የሰውነት መቆጣት፤ የአይን መቅላት፤ ትኩሳት እና መሰል ህመሞች የታየባቸው ሲሆን ሁሉም ወደ ሀክምና መወሰዳቸው ተገልጿል።
የአልጀሪያ አካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር የጉዳዩን ምንነት ለመለየት የውሃ እና አየር ናሙናዎችን ወስዶ በመመርመር ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ይሁንና ጉዳዩን እንዲመለከቱ ወደ ቦታው የተላኩ 28 ሰዎች ደግሞ ህመም ማሳየታቸው ተገልጿል።