የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በኦንላይን መሰጠቱ ቀረ
ሚኒስቴሩ ከአሁን ቀደም ከ4 መቶ ሺህ የሚልቁ ታብሌት ኮምፒውተሮችን ከውጭ ለመግዛት በሚያስችል ሂደት ላይ እንደነበር ማስታወቁ የሚታወስ ነው
የኦን ላይን ፈተናው የቀረው የመፈተኛ ታብሌት ኮምፒውተሮች በወቅቱ ሃገር ውስጥ ለመግባት ባለመቻላቸው ነው
በኦን ላይን ሊሰጥ የነበረውን የ2012 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በወረቀት ማድረጉን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ይህን ያደረገው የመፈተኛ ታብሌት ኮምፒውተሮች በወቅቱ ሃገር ውስጥ ለመግባት ባለመቻላቸው ነው፡፡
በመሆኑም ፈተናው በያዝነው ወር መጨረሻ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም በወረቅት እንደሚሰጥ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
ተፈታኞች የፈተና መግቢያ መታወቂያ በየትምህርት ቤታቸው ከየካቲት 22 እስከ 24 ድረስ ያኛሉም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ከየካቲት 21 እስከ 27 የፈተና እና የመልስ መስጫ ወረቀቶች ወደ ዞኖች እንደሚደርሱም ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ሃገር አቀፍ ፈተናውን ተማሪዎችን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭነት ሊጠብቅ እና ኩረጃን ሊያስቀር በሚችል መልኩ እሰጣለሁ በሚል ዝግጅቶችን ሲያደርግ ነበር፡፡
ከሰሞኑ የፈተናውን ቀን ቆርጠው እንዲያሳውቁ ላሳሰባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ-አደር እና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ከ4 መቶ ሺህ የሚልቁ ታብሌት ኮምፒውተሮችን ግዢ በመፈጸም ወደ ሀገር ለማስገባት በሂደት ላይ ነን ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡