ዓለም በ2020 ያስተናገደቻቸው ዐበይት ክስተቶች
በዓመቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ ሌሎችም ክስተቶች በዓለም ፖለቲካና ማህበረ-ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል
እጅግ አስከፊ ከሆኑ ዓመታት ጎራ በሚመደበው 2020 ኮሮና ዓለምን የፈተነ ዋነኛ ጉዳይ ነው
በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ 2020 ዓለማችን በርካታ ፈተናዎችን አስተናግዳለች፡፡ በዓመቱ ዋዜማ ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ደግሞ በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች ፣ የአሜሪካ ምርጫ ፣ የፍሎይድ ግድያ እና የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ስምምነትም ከዐበይት የ2020 ሁነቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
1 / ኮሮና ቫይረስ
ከዓመት በፊት ፣ 2019 ተጠናቆ 2020 ሊገባ ቀናት ሲቀሩት የታህሳስ ወር መገባደጃ ለ2020 አስከፊ ክስተትን ጥሎ ነው ያለፈው፡፡
በታህሳስ ወር በቻይና ዉሀን ከተማ የተከሰተው ዓለም እንደ አዲስ የተዋወቀችው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) መላውን ዓለም ለማዳረስ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ አሜሪካ፣ሕንድ፣ብራዚል፣ሩሲያ እና የአውሮፓ ሀገራት ቫይረሱ በፍጥነት ተዛምቶባቸዋል፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ሀገራትም በወረርሽኙ ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡
በፍጥነት በመዛመት ላይ የሚገኘው ቫይረሱ በአንድ ዓመት እድሜው ከ 83 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የያዘ ሲሆን ከነዚህም ከ1 ሚሊዮን 813 ሺ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ወደ 59 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ከፍተኛ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡም ይታወቃል፡፡ ተሰናባቹና ተመራጩ ፕሬዚዳንቶች ሲከራከሩበት የነበረው ይህ ወረርሽኝ፤ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው የነበሩት ትራምፕ ለቫይረሱ ትኩረት አልሰጡትም ተብለው በአሜሪካውያን፣ በሕክምና ባለሙያዎችና በሌሎች የዓለም ክፍሎች በሚኖሩ ነዋሪዎች ሲተቹ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ስለ ቫይረሱ ዓለም በቂ መረጃ እንዲያገኝ አላስቻለም በማለት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና ጋር ወግኗል ካሉት የዓለም ጤና ድርጅት ሀገራቸው እንድትወጣም አድርገዋል፡፡ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ምርጫውን እንዲያሸንፉ ያደረጓቸው ዋነኛ ምክንያቶች የቫይረስ ንክኪ ልየታ መዘርጋት፣ በአሜሪካ ግዛቶች የመመርመርያ ማዕከላትን ማቋቋም፣ ለሁሉም ነፃ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማድረግ እና ክትባት በብዛት ማቅረብ የሚሉት መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ቫይረሱ የዓለምን ፖለቲካዊ እና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ስርዓቶች አዛብቷል፡፡ ዓመቱን ሙሉ ዓለም የተፈተነችበት ይህ ቫይረስ የተለያዩ ክትባቶች ተገኝተውለት ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ አንዳንድ የበለጸጉ ሀገራት ለዜጎቻቸው ክትባቱን መስጠት ጀምረዋል፡፡ ድሃ ሀገራት ክትባቱን ለማግኘት ረዥም ጊዜ መጠበቅ ግድ የሚላቸው ሲሆን ከቆይታ በኋላም ቢሆን በነዚህ ሀገራት ክትባቱን ሊያገኝ የሚችለው አነስተኛ ህዝብ እንደሆነ ይጠበቃል፡፡
2020 ደግሞ በመሰናበቻው ለ2021 ሌላ የቤት ሥራ ትቶ በማለፍ ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ በብሪታንያ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የተገኘ ሲሆን የስርጭት መጠኑ ከቀድሞው ቫይረስ 70 በመቶ እንደሚልቅ የተነገረለት ይህ አዲሱ ዝርያ በተለያዩ ሀገራትም ተከስቷል፡፡
2 / የፍሎይድ ግድያ እና ዓለም አቀፍ መዘዙ
በአሜሪካ ጥቁር አፍሮ አሜሪካውያን ኢፍትሀዊ በሆነ መንገድ በፖሊስ ሲገደሉ መስማት የተደጋገመ እና የተለመደ ክስተት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ የ46 ዓመት ጥቁር አሜሪካዊ በሚኒያፖሊስ በ 4 ፖሊሶች መገደሉም በ2020 ብዙ መዘዞችን ያስከተለ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ ፖሊሶቹ ጆርጅ ፍሎይድን ሰነድ አጭበርብሯል በሚል በሚኒያፖሊስ ከተማ አደባባይ ላይ ይዘውት ከመኪናው በማውረድ ከእነርሱ መኪና በታች አስፓልት ላይ ያስተኙታል፡፡ ከዚያም ከፖሊሶቹ አንዱ በጉልበቱ አንገቱ ላይ ተንበርክኮ ከ8 ደቂቃ በላይ በመቆየት ለህልፈት ዳርጎታል፡፡ ይህንን ተከትሎ የ ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ (Black Lives Matter) እንቅስቃሴ በአሜሪካ ግዛቶችና በመላው ዓለም ተስተጋብቷል፡፡ የጥቁሮች መብት ይከበር፤ ፍትሕ ለጆርጅ ፍሎይድ የሚሉ ዘመቻዎች ከአሜሪካ አልፈው በበርካታ ሀገራት ጎዳናዎች ተካሂደዋል፡፡ በአሜሪካ የተፈጸመው የጥቁር ሰው ግድያ ሌሎች ሀገራትም ላይ የሚገኙ ጥቁሮች የሚፈጸምባቸውን የዘረኝነት ጥቃት ለማውገዝ በር ከፍቷል፡፡
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና ሌሎች በርካታ ስመጥር ሰዎችም ድርጊቱን በመኮነን በፖሊሶቹ ላይ አስፈላጊው ምርመራ በፍጥነት ተደርጎ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ “ጆርጅ ፍሎይድ እና ቤተሰቦቹ ፍትህ ያስፈልጋቸዋል” ያሉት ጆ ባይደን ፖሊሶቹ ከስራቸው እንዲሰናበቱ መደረጉን ማድነቃቸው ይታወሳል፡፡ የነጭ የበላይነትን በመደገፍ የዘረኝነት አቋም የሚተቹት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ አቋማቸው አሜሪካን እንደከፋፈሉም ይታመናል፡፡ በምርጫው ወቅት ዋነኛ አጀንዳ ከነበሩ ጉዳዮችም አንዱ ይኸው የዘረኝነት ጉዳይ ነበር፡፡
3 / የአሜሪካ ምርጫ 2020
የአሜሪካ ምርጫ 2020 የአሜሪካውያንን ብቻ ሳይሆን ፣ የግል ጉዳይ እስኪመስል ድረስ የመላውን ዓለም ቀልብ የያዘ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ሀገሪቱ በዓለም ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ላይ ያላት ተጽእኖ ብቻ ሳይሆን ከትራምፕ የ ’አሜሪካ ትቅደም’ መርህን የተከተለ አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችም ጭምር ናቸው፡፡
ከ 159 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጽ የሰጡበት የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን ከኋይት ሃውስ አሰናብቷል፡፡ በዚህ ምርጫ ጆ ባይደን 81 ሚሊዮን 283 ሺ 98 (51. 3 በመቶ ) ድምጽ በማግኘት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ ይህን ያህል ድምጽ በማግኘት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሲኮን በታሪክ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በዕድሜ ትልቁ የአሜሪካ መሪም በመሆን ባይደን ክብረወሰን ይይዛሉ፡፡ ዶናልድ ትራምፕ 74 ሚሊዮን 222 ሺ 957 (46.7 በመቶ) ድምጽ በማግኘት ቢሸነፉም በታሪክ ሁለተኛውን ከፍተኛ ድምጽ አግኝተዋል፡፡
ምርጫው ከተካሄደ በኋላ በየግዛቱ በጥቂት ተወካዮች በሚካሔደው የውክልና ድምጽ ምርጫ ከ538 የውክልና ድምጾች 306 ድምጽ በማግኘት ጆ ባይደን በይፋ 46ኛ ፕሬዝዳንትነታቸው ተረጋግጧል፡፡‘ኤሌክቶራል ኮሌጅ’ የሚል ስያሜን በያዙት በእነዚህ የውክልና መራጮች ከሚሰጠው ድምጽ ውስጥ 270 እና ከዚያ በላይ የሚሆነውን ማግኘት ለአሸናፊነት የሚያበቃ ሲሆን ባይደን በዋናው ምርጫ ያገኙትን ያክል 306 ድምጽ አግኝተዋል፡፡ ጆ ባይደን በዶናልድ ትራምፕ ተበላሽተው የነበሩ የኢራን የኒዩክለር ስምምነት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ፤የዓለም ጤና ድርጅትና ሌሎንም ለማስተካከል ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ዴሞክራቱ ባይደን ምርጫውን ቢያሸንፉም ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን እስካሁን ሽንፈትን አላመኑም ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን በፈረንጆቹ ጥር 20 ባይደን ወደ ቤተ መንግስት እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
4 / የመካከለኛው ምስራቅ ሰላም
በ አውሮፓውያኑ 2020 ከተከናወኑ አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱና ብዙ ትኩረትን የሳበው ፣ እስራአል ከአረብ ሀገራት ጋር የሰላም ስምምነት በመፈጸም የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጀመሯ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ከዓረብ ሀገራት መካከል ከግብፅ እና ከዮርዳኖስ ጋር ብቻ መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የነበራት እስራኤል በ2020 በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በር ከፋችነት ከአራት ሀገራት ጋር ስምምነት ፈጽማለች፡፡
እስራኤል ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ባህሬንና ሞሮኮ ጋር ያደረገችው የሰላም ስምምነት በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ነበር፡፡ እስራኤል ከሱዳን ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ስምምነት ላይ ደርሳለች፡፡
ስምምነቱ የቀጣናውን ህዝቦች ፍላጎቶች ለማሟላት ፣ ለሰላምና መረጋጋት መስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል፡፡ በተለይም የኢኮኖሚ ፣ የባህልና የእውቀት ግንኙነቶችን ለማጠናከር መንገድ የሚከፍት በመሆኑ ፣ የቀጣናውን ህዝቦች የብልፅግና እና የለውጥ መሻት እንደሚያረጋግጥም ነው የታመነው፡፡
የእስራኤል መንግስት ካቢኔ እና ክኔሴት (ፓርላማው) በመስከረም ወር አጋማሽ በዋሺንግተን ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ያጸደቀ ሲሆን በፓርላማው አባላት ሰፊ ተቀባይነት ማግጠቱም የሚታወስ ነው፡፡ ከባህሬን ጋር የተደረሰውንም ስምምነት እንዲሁ ፓርላማው አጽድቆታል፡፡ ዩኤኢ እና ባህሬንም እንዲሁ ከእስራኤል ጋር የተደረሰውን ስምምነት አጽድቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እስራኤል ከሌሎች የዓረብ ሀገራት ጋር ስምምነት እንደምታደርግም ፍንጭ መስጠቷ ይታወሳል፡፡
5 /ኢራን፡ የሱሌማኒ ግድያ እና የዩክሬን አውሮፕላን መጋየት
በፈረንጆቹ ጥር 3 ቀን 2020 በኢራናውያን የሚከበሩትና የሀገሪቱን መንግሥት ደህንነት በማስጠበቅ ቁልፍ ሚና የነበራቸው የኢራን ከፍተኛ ጄኔራል ቃሲም ሱሌማኒ መገደላቸው አንዱ የ 2020 ትልቅ ክስተት ነበር፡፡
በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሰበር ዜና የነበረው የሜ/ጄኔራል ሱሌማኒ መገደል፣ በኢራናውያን ቁጣን ሲቀሰቅስ፣ ለተቀረው ዓለም ደግሞ ሥጋትን አጭሮ ነበር፡፡
የ62 ዓመቱ ሜጀር ጄኔራል ሱሌማኒ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚከናወኑ ወታደራዊ ዕርምጃዎች ግንባር ቀደም የነበሩ ሲሆን፣ ባግዳድ አየር ማረፊያ ውስጥ ከሌሎች በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች ጋር ባሉበት ነበር በአሜሪካ የአየር ጥቃት መገደላቸው የተገለጸው፡፡ ለጁምአ ፀሎት የወጡ ኢራናውያን የሱሌማኒን መገደል ከሰሙ በኋላ ደረታቸውን እየደቁ፣ እንባቸውን እየረጩ ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
የሱሌማኒ መገደል ቀድሞውንም በቋፍ የነበረውን የዋሸንግተንና ቴህራን ግንኑነት ወደባሰ ችግር ውስጥ እንዳስገባው ይታወሳል፡፡ ኢራን በወሰደችው አጸፋዊ እርምጃ ፣ በኢራቅ የሚገኘውን የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፕ በባለስቲክ ሚሳይል ደብድባለች፡፡ 176 ሰዎች የሞቱበትን የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላንም ያጋየች ሲሆን በአሜሪካ ካምፕ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የወሰደችው ይህ እምጃ በስህተት መከናወኑን ሀገሪቱ አስታውቃለች፡፡
ቀድሞውንም በዘመነ ባራክ ኦባማ ተደርሶ የነበረውን የኑክሌር ስምምነት ቀደው የጣሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀቦችንም ጥለዋል፡፡
6 / የተፈጥሮ አደጋዎች
በተጠናቀቀው 2020 የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎችም በመላው ዓለም ተከስተዋል፡፡ ዩኤስ አሜሪካን እና የማዕከላዊ አሜሪካ ሀገራትን ያጠቃው የአትላንቲክ አውሎ ንፋስ ከ400 በላይ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል፡፡ በአጠቃላይ ከ40 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ንብረትም አውድሟል፡፡ በቻይና የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ጎርፍ ደግሞ ከ200 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን ከ32 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ ህንድም በጎርፍ አደጋ የተመታች ሲሆን በተጨማሪም ከሰሪ ላንካ እና ባንግላዴሽ ጋር በአውሎ ነፋስም ተመታለች፡፡ ጃፓን እና ፓኪስታንም የጎርፍ አደጋ አስተናግደዋል፡፡
የብዙዎችን ህይወት የቀጠፉ እና በርካታ ጉዳቶችን ያደረሱ ተፈጥሮ አደጋዎች በበዙበት በተጠናቀቀው ዓመት በምስራቅ አፍሪካ በአንበጣ መንጋ ወረርሽን 9 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የሰብል እና የመኖ ውድመት ደርሷል፡፡ አሜሪካ እና አውስትራሊያ በከፍተኛ መጠን የሰደድ እሳት ሲጠቁ እንደ ኤሲያ እና የአሜሪካ ሀገራት ሁሉ አውሮፓም በአውሎ ነፋስ ተመታለች፡፡
7 / የቤሩቱ ፍንዳታ
እ.ኤ.አ. ነሓሴ 4/2020 በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት ወደብ ላይ የደረሰው ከባድ ፍንዳታ ከ200 በላይ ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ፤ ከ6 ሺ በላይ መቁሰላቸውን የሚታወስ ነው፡፡ ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተያይዞ ጎዳናዎች ላይ ውሎ ማደርን ልምዳቸው ያደረጉት የሀገሪቱ ዜጎች ፣ በዚህ ከባድ አደጋ ጊዜም አደባባይ በመውጣት ሀገሪቱ ለገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ መንግስትን ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ የቤሩት ነዋሪዎች የሀገሪቱ መሪዎች ስልጣናቸውን እንዲለቁ የጠየቁ ሲሆን ሊባኖስን በወቅቱ የጎበኙት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ማክሮንም የሀገሪቱ ባለስልጣናት ከኃላፊነት እንዲነሱ ጫና ያሳድሩ ዘንድ ሰልፈኞቹ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ፍንዳታው ለደረሰበት አካባቢ መልሶ ግንባታ እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ መግለጻቸው የሚታወስ ቢሆንም በከፍተኛ የገንዘብ ችግር ዉስጥ ለምትገኘው ሊባኖስ ይህ እጅግ ፈታኝ ጥያቄ ነው፡፡ ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ የምዕራቡ አለም እና የገልፍ ሀገራት ለመልሶ ግንባታ ድጋፍ ሊያደርጉላት ቃል ገብተዋል፡፡
8/ ብሬግዚት
ብሪታንያ ከአውሮፓ ሕብረት የተፋታችውም በዚሁ በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ 2020 ነው፡፡ የፍቺ ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ 3 ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ያስተናገደችው ብሪታንያ በስተመጨረሻ ለ47 ዓመታት ከቆየችበት የአውሮፓ ሕብረት በቦሪስ ጆንሰን መሪነት ጥር 31/2020 ወጥታለች፡፡
የአውሮፓ ሕብረትና ብሪታንያ ከተፋቱ (ብሬግዚት) በኋላ በሚኖራቸው የንግድ ግንኙነት ላይ ባለፈው ሳምንት ከስምምነት መድረሳቸውም ታውቋል፡፡
የሕብረቱ ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ለየን ብራሰልስ እና ለንደን በረጅምና ሰፊ የድርድር መንገድ ቢያልፉም ለሁለቱ ወገኖች ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ ከሆነ የንግድ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡