የ2012ቱ ሃገር አቀፍ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ነሃሴ 10 እንዲሆን ሃሳብ ቀርቧል፡፡ በቀረበው ሃሳብም ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ሁኔታና ምርጫ 2012
በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ምርጫ በየ5 ዓመቱ ይደረጋል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢህአዴግ) የአሁኑ ብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ መንግስ ከመሰረተ ወዲህ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ ምርጫ ይካሄዳል፡፡
ይሁንና በዚህ ዓመት ይደረጋል የተባለው ምርጫ በበርካታ ውጣ ውረዶች የታጀበና ፓርቲዎቹም ቢሆኑ ምርጫው ይካሄድ አይካሄድ በሚል የተለያዩ ሃሳቦች የሚነሱበት ነው፡፡
የምርጫውን የጊዜ ሰሌዳ እና አፈፃፀም በተመለከተ ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የሲቪክ ማህበራት፣የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮችና የአካል ጉዳተኞች ማህበር ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
ምርጫውን የተመለከተ የጊዜ ሰሌዳ ያቀረበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫው ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ/ም እንዲካሄድ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ ሆኖም ምርጫው የሚደረግበትን ዕለት ጨምሮ ሌሎች የወጡ መርሃ ግብሮች በረቂቅ ደረጃ እንጂ የመጨረሻ እንዳልሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የቀረበውን ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በማድረግ በተደረገው ውይይትም የተለያዩ አስተያየቶች በዋናነት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተሰጥተዋል፡፡ ከተሰጡት አስተያየቶች መካከልም
ለመራጮች የምዝገባ ጊዜ 30 ቀን ያንሳል ፤ቢታሰብበት!
የምርጫው ጊዜ ክረምት መሆኑ ለማስፈፀም ያስቸግራል፣ ለምን ጥቅምት/ህዳር ላይ አይሆንም?
በምርጫ ዘመቻ ወቅት ወከባ እንዳይፈጠር ቦርዱ ምን ዝግጅት አድርጓል?
የምረጡኝ ቅስቀሳ ቀናት ያንሳሉ፣ ከአሁን ጀምሮ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎችም አሉ፣ ቦርዱ ምን ይላል?
ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ የሚደረደሩበት ቅደም ተከተል በእጣ ይሆናል ማለት ምን ማለት ነው?
የቦርዱ የአመራር አካላት ምላሽ
የመራጮች ምዝገባ በህግ የተቀመጠ 30 ቀን ነው።
የእጩ ምዝገባ ቀናት በህግ የተቀመጠ መልኩ ይታያል፣ አስፈላጊ ከሆነ ቀን መጨመሩን ቦርዱ ሊያየው ይችላል ፡፡ ነገር ግን በዕቅዱ ላይ የተቀመጠው ቀን ለፓርቲዎች አያንስም እንዲያውም ጫና የሚሆነው ለቦርዱ ነው።
ነሃሴ ላይ ምርጫው መካሄዱ ቦርዱ ወዶ የገባበት አይደለም፤ግንቦት ለማድረግ ስላልተቻለ ነው፡፡ ብዙ የተዘረዘሩ ለውጦች እያደረገ እንደሆነ ቦርዱ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ስለዚህ ግንቦት ላይ ማድረግ የሚቻል አይደለም። አፈፃፀሙ ክረምት በመሆኑ ብዙ ችግር እንደሚገጥመው የታወቀ ነው ነው ከክልል መንግስታት፣ ከፌደራል መንግስትና ሌሎች ተቋማት ቦርዱ የሎጀስቲክስ ድጋፍ ጠይቆ ለማስፈፀም ጥረት ያደርጋል። ከመስከረም ካለፈ ደግሞ የህግ ጥሰት ስለሚፈጠር ወደፊት መግፋት አልተቻልም፡፡
የዘመቻ ጊዜ ከወከባ እና ችግር እንዳይኖር ቦርዱ ጥረት ያደርጋል፡፡ከዚህ በፊት ፓርቲዎች ችግር ሲገጥማቸው ቦርዱ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፤ አሁን ይህንን ድጋፉን ለማስፋት በምርጫ ዘመቻ ወቅት የራሱን ዴስክ አዘጋጅቶ ተቋማዊ ድጋፍ ያደርጋል።
የምረጡኝ ቅስቅሳ አሁን መጀመር አይቻልም፣ የተሰጠው 3 ወር ከበቂ በላይ ነው፡፡ ከአሁኑ ቅስቀሳ የጀመሩ አሉ ለተባለው ውይይት እና ንግግር ከህዝብ ጋር ማድረግ ይቻላል፤ እኔን ምረጡኝ የሚል ዘመቻ ግን መጀመር አይቻልም፣ ያንን የሚያደርጉ ፓርቲዎች ላይ ቦርዱ ማጣራትን በማድረግ የራሱን እርምጃ ይወስዳል፡፡
በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የፓርቲዎችቅደም ተከተል በእጣ ይሆናል ሲባል ከዚህ በፊት እንደነበረው እንዳይሆን ለማድረግ ነው። እጣው ላይ በሚደርሳቸው ቅደም ተከተል መሰረት ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ በቅደም ተከተል ይቀመጣሉ።
ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ተወካይ አቶ ልደቱ አያሌው በዚህ ዓመት ምርጫን ማድረግ አያስችልም የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ በሃገሪቱ ያለው አለመረጋጋት እና በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የጸጥታ ችግር ምርጫ ለማከናወን አያስችልም ሲሉም ነው አቶ ልደቱ ሃሳብ የሰጡት፡፡ ከዚህ ባለፈም ለምርጫ አስፈጻሚነት የሚመለመሉ 250ሺ ሰዎችን፣የታዛቢዎች እና የሌሎችም ገለልተኛ ነት ምን ያህል ነው የሚለውን ከማረጋገጥ ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ ዶ/ር አለሙ ስሜ በበኩላቸው አሁን ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው ለዚህም ሁሉም ፓርቲዎች ቁርጠኛ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የሃገሪቱን ጸጥታ የሚከታተል ዴስክ ማቋቋሙን አስታዉቆ በዚሁ ጉዳይ ላይ ሌላ ጊዝ ዉይይት አንደሚደረግ አስታዉቋል፡፡ ለምርጫው 250 ሺ ታዛቢዎች እንደሚያስፈልጉና ገለልተኝነታቸው እንደሚረጋገጥም ነው የገለጸው፡፡