2012 የህዳሴ ግድብ የዉሃ ሙሌት እና የበርካታ ንጹኃንን ግድያ ጨምሮ በርካታ ክስተቶችን አስተናግዷል
የ2012 ዓ.ም አበይት ክስተቶች በኢትዮጵያ
የተጠናቀቀው 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ክስተቶችን ያስተናገደችበት ነው፡፡ በሀገሪቱ ከተከሰቱ አበይት ሁነቶች ደግሞ የህዳሴ ግድብ የዉሃ ሙሌት ፣ ኮሮና ቫይረስ ፣ የንጹሀን ሰዎችን ግድያና መፈናቀል ጨምሮ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውሶችን ያስከተሉ አሳዛኝ እና አስከፊ ክስተቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህን እና መሰል በዓመቱ ውስጥ የተከሰቱ ዋና ዋና ክስተቶች አል ዐይን አማርኛ እየተከታተለ ሲዘግብ ቆይቷል፡፡
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና መዘዙ
በአስከፊነቱ በሚታወቀው በ 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ ካስተናገደቻቸው አሳዛኝ ክስተቶች ባለፈው ሰኔ ወር የተፈጠረው የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና ይህን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ የተፈጸመው የበርካታ ንጹሀን ሰዎች መገደል ወደር የማይገኝለት ነው፡፡
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ገላን አካባቢ ምሽት 3 ሰዓት ገደማ በግል ተሸከርካሪው ውስጥ እያለ በተተኮሰበት ጥይት ነበር ዝነኛው የኦሮምኛ አቀንቃኝ ሀጫሉ ሁንዴሳ የተገደለው፡፡ የአርቲስቱ ሞት በብዙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ቁጣ ቀስቅሶ ለሌሎች በርካታ ንጹሀን ዜጎች ያለሀጢያታቸው መገደል ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይም በምዕራብ አርሲ ፣ በሀረርጌ እና በአዲስ አበባ በተፈጸመው ጥቃት በትንሹ 229 ሰዎች መሞታቸውን መንግስት አስታውቋል፡፡
በርካታ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች ፣ ተሸከርካሪዎች እና የተለያዩ ንብረቶችም ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ወድመዋል፡፡
የሀጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ሁከት ከተፈጠረው እልቂት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ በርካታ ፖለቲከኞች እና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ በኦሮሚያ ክልል በደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት የተጠረጠሩ ከ7,100 በላይ ግለሰቦች በፖሊስ መያዛቸውን ለአል ዐይን አማርኛ በወቅቱ ገልጸው ነበር፡፡
ይህ ክስተት በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ እንዲቆይም ምክንያት ሆኗል፡፡ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ለ15 ቀናት የሞባይል ደግሞ ለ23 ቀናት ተዘግተው ከቆዩ በኋላ ነው የተለቀቁት፡፡
“የጃዋር ጠባቂዎች ይነሱ” መባል ያስከተለው እልቂት
በ2012 ዓ.ም ጥቅምት ወር መገባደጃ ላይ የአቶ ጃዋር መሀመድ ጠባቂዎች በድብቅ እንዲነሱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል በሚል በኦሮሚያ ክልል ፣ በሐረሪ ክልል እና በድሬዳዋ ተከስቶ በነበረው ሁከት የ86 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
በሁከቱ የተፈጠረውን የሰዎች ሞት በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሰጡት መግለጫ ከሟቾቹ 76ቱ እርስ በእርስ በተፈጠረ ግጭት እንዲሁም 10 ሰዎች ደግሞ በጸጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ ህይወታቸው ማለፉን አመልክተዋል።
ከዚህ ክስተት በኋላ መንግስት የዜጎችን እና የሀገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢገልጹም ከዚያ በኋላም በርካታ አለመረጋጋቶች ተከስተዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ተጽእኖው
በታህሳስ ወር በቻይና ዉሀን የተከሰተው ዓለም እንደ አዲስ የተዋወቀችው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) መላውን ዓለም ለማዳረስ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ኢትዮጵያም ቫይረሱ ከተከሰተ 4 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መጋቢት 14 የመጀመሪያውን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ አገኘች፡፡
በወቅቱ በአንድ ጃፓናዊ ላይ የተገኘው ይህ ቫይረስ አንድ ሁለት እያለ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ60 ሺ በላይ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ 950 ያህል ሰዎችም ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡
ቫይረሱ በሀገሪቱ ማህበረ ኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርዓት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡
ቫይረሱ በቻይና ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ሂደቱን በመከታተል ሲዘግብ የቆየው አል ዐይን አማርኛ በመላው ዓለም እና በኢትዮጵያ የቫይረሱን ስፋት እና ተጽእኖውን እንዲሁም ሊደረጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች በተለያዩ ጊዜያት ዘግቧል፡፡
ቫይረሱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ተመሳሳይ ሊባል የሚችል ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ በርካቶችን ከስራ ገበታቸው አፈናቅሏል ፤ በህዝብና በመንግስት ላይ ከፍተኛ የማህበረ ኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሏል፡፡ ኢትዮጵያ ያለፉትን 5 ወራት በአስቸኳይ ጊዜ ዉስጥ ስታሳልፍ ፣ የስራ ሰዓት ሽግሽግ ተደርጓል ፤ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል ፤ የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና ሁሉም ስፖርታዊ ዉድድሮች ተቋርጠዋል፡፡
በተለያዩ ሀገራት በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ተከትሎ የተለያዩ ፖለቲካዊ ቀውሶችም ተከስተዋል፡፡
የምርጫ መራዘም እና የትግራይ ክልላዊ ምርጫ
በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርጫ 2012 እንዲራዘም አድርጓል፡፡ ቀድሞውንም በበርካታ የፖለቲካ ውጥረት ዉስጥ ሆና ፣ ብዙ ፈተናዎች እንደተጋረጡባት ነሐሴ 23 ምርጫ ለማድረግ ቀን የቆረጠችው ኢትዮጵያ በቫይረሱ መከሰት ምክንያት በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት ምርጫው እንዲራዘም ወስናለች፡፡ ምርጫው የኮሮና ቫይረስ አሳሳቢ አለመሆኑ በዓለም ጤና ድርጅት እና በጤና ሚኒስቴር ከተረጋገጠ በኋላ በአንድ ዓመት ጊዜ ዉስጥ እንዲካሔድ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡ ይህ ሂደት ታዲያ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ምርጫው ይራዘም ወይስ አይራዘም ከተራዘመስ በምን መልኩ መሆን አለበት የሚለው እጅግ አጨቃጫቂ እና ዛሬም ድረስ መግባባት ያልተደረሰበት ሁነት ነው፡፡
ከምርጫው ጋር በተያያዘ የተፈጠረው አለመግባባት ተካርሮ የትግራይ ክልል በተናጠል ምርጫ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቆ ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ክልላዊ ምርጫ አድርጓል፡፡
የትግራይ ምርጫ ከመካሔዱ ከ4 ቀናት በፊት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰበ በክልሉ የሚደረገው ምርጫ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር መሆኑን በመግለጽ ምርጫው ቢደረግም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረገ እንደሚቆጠር እና ተቀባይነት እንደማይኖረው ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በምርጫው ምክንያት የትግራይ ክልል እና የፌዴራሉ መንግስት ፍጥጫ ከመርገብ ይልቅ ይበልጥ እየተካረረ መምጣቱ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ መጻኢ ዕድል ፈንታ ለብዙ ትንታኔዎች አጋልጧል፡፡
የተማሪዎች እገታ
በብዙ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ 16 ዩኒቨርሲቲዎች በተደጋጋሚ በተማሪዎች መካከል ግጭቶች እና ሌሎች ችግሮች ተፈጥረው የተማሪዎች ህይወት አልፏል፡፡
ከነዚህ ዩኒቨርሲቲዎችም ከ35 ሺ በላይ ተማሪዎች ወደ ቤተሰባቸው አሊያም ወደ ሌሎች አካባቢዎች ዩኒቨርሲቲዎችን ለቀው ስለመሔዳቸው መንግስት በወቅቱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ ከዩኒቨርስቲው ወጥተው ወደ ቤተሰባቸው ሲሄዱ ታገቱ የተባሉ ተማሪዎች ጉዳይ ደግሞ አሁንም ድረስ እልባት ያላገኘ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል፡፡
ከ2012 ዓ.ም አበይት ክስተቶች አንዱ የሆነው በወርሃ ህዳር የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ታገቱ የተባሉት ተማሪዎች ቁጥር አንድ ጊዜ 17 ሌላ ጊዜ 27 እየተባለ በተለያዩ አካላት ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ስለ ታጋቾቹ እና ስለሚገኙበት የጠራ መረጃ እስካሁን ባይገኝም በዚህ እገታ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በክስ ሂደት ላይ ስለመሆናቸው ጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጹ ይታወቃል፡፡
የህዳሴው ግድብ የዉሀ ሙሌት
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 10 ዓመታት በኢትዮጵያ ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል በግድቡ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ባለፈው ዓመት ይበልጥ ተጠናክሮ ሲካሔድ ቆይቷል፡፡ የአሜሪካ እና የዓለም ባንክ በድርድሩ ጉዳይ መግባት ደግሞ ሂደቱን ይበልጥ አወሳስቦታል፡፡
መቋጫ ያልተገኘለት ድርድሩ ያለስምምነት እንደቀጠለ 2012 ቢጠናቀቅም የግድቡ የመጀመሪያ ዓመት የዉሃ ሙሌት መከናወኑ ግን ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ብስራት ነው፡፡
የመጀመሪያው ዓመት የዉሃ ሙሌት ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በእለቱ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያመጠቀችው ሳተላይት
2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ያመጠቀችበት ዓመትም ነው፡፡
ታህሳስ 10 ከቤጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የቻይና ጠፈር ምርምር ማዕከል የመጠቀችው ETRSS-1 የሚል ስያሜ የተሰጣት ሳተላይቷ የታሰበላትን ቦታ ይዛ ስራዋን በአግባቡ እየሰራች መሆኑ ከቀናት በኋላ ተገልጿል።
ሳተላይቷ በቀን አስራ አራት ጊዜ በተዘጋጀላት ምህዋር እየዞረች መረጃ የምትሰበስብ ሲሆን በቀን አራት ጊዜ ደግሞ የሰበሰበችውን መረጃ የመቀበል ስራ ይሰራል፡፡
በኢትዮጵያ የታየው የፀሀይ ግርዶሽ
እሁድ ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ፀሐይ ከ60 እስከ 99 በመቶ ተሸፍና ከከፊል ቀለበታማ ግርዶሽ ታይቷል፡፡
በሌሎች አንዳንድ የዓለማችን ክፍሎችም በዕለቱ የፀሀይ ግርዶሽ ታይቶ የነበረ ቢሆንም ግርዶሹን በሙላት ለማየት እንደኢትዮጵያ አመቺ ስፍራ እንዳልነበረ የዘርፉ ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በዓለም የፀሐይ ግርዶሽን ለማየት 18 ዓመታትን እንደሚወስድ የዘርፉ ባለሙያ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ደግሞ የአሁኑን አይነት የፀሐይ ግርዶሽ ለማየት ከ140 በላይ ዓመታትን መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ
የተጠናቀቀው 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በፌደራል ስርዓት ውስጥ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት በህዝበ ውሳኔ አዲስ ክልል የተመሰረተበት ዓመትም ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን በህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም አስፈጽሞ ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ያሳወቀ ሲሆን የመጨረሻ ውጤቱን ደግሞ ሕዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም አሳውቋል፡፡ በዚህም መሰረት ሲዳማ በህዝበ ውሳኔዉ ድምጽ ከሰጡ መራጮች ከ98% በላይ የሚሆኑት ሲዳማ ክልል እንዲሆን ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
በ5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ የሲዳማ ክልል ስልጣን አስረክቧል፡፡
ከደቡብ ክልል ጋር የመለያየት ሂደቶች አጠናቅቆ ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ስልጣን የተረከበው የሲዳማ ክልል ሰኔ 27 ቀን 2012ዓ.ም. በይፋ ክልል ሆኖ ተመስርቷል፡፡
ይሁን እንጂ በደቡብ ክልል ዛሬም ድረስ ያልተፈቱ ተመሳሳይ የክልልነት ጥያቄዎች በብዛት በመነሳት ላይ ናቸው፡፡ ይህም ለፌዴራሉ መንግስት የ2012 አንዱ ፈተና ሆኖበት ነው ያለፈው፡፡
በዓመቱ መገባደጃ ላይ ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በዎላይታ ዞን በተፈጠረው ቀውስ የሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ ለችግሩ መከሰት ምክንያት ናቸው የተባሉ ፣ የዞኑን አስተዳዳሪ ጨምሮ የተለያዩ አመራሮች ከስልጣናቸው ተነስተው የክስ ፋይል ተከፍቶባቸዋል፡፡ አዲስ የዞን አስተዳዳሪም በዞኑ ምክር ቤት ተመርጦ በቅርቡ ስራ ጀምሯል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኖቤል ሽልማት
የአውሮፓውያኑ የ2019 የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኖቤል ሽልማታቸውን በጥቅምት ወር የመጀመሪያ ቀን 2012 ዓ.ም በኖርዌይ ኦስሎ በተካሄደ ደማቅ ስነ ሥርአት ተቀብለዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የኖርዌይ ንጉሳውያን ቤተሰብ አባላት፣ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ በሀገሪቱ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የተለያዩ ታዳሚያን ተገኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን ያሸነፉት ለሰላም እና አለማቀፍ ትብብር ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሆነ የሽልማት ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ቤሪት ሬይስ አንደርሰን እንዳሉት በተለይም የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ለ20 ዓመታት የቆየ የድንበር ውዝግብ ለመፍታት የወሰዱት ቆራጥ ውሳኔ ሽልማቱን ለማሸነፋቸው ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡
ሌሎች ክስተቶች
የተጠናቀቀው 2012 ዓ.ም ከላይ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ክስተቶች ጨምሮ በርካታ አስከፊም አስደሳችም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ክስተቶች የተስተናገዱበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡
በዓመቱ ከተስተዋሉ በርካታ ክስተቶች መካከል የኢህአዴግ በውህደት መክሰም እና የብልጽግና ፓርቲ ገዢ ፓርቲ ሆኖ መመስረት ፣ የአምበጣ መንጋ ወረርሽኝ ፣ የ10 ሰዎች ህይወት ያለፈበት በጎንደር የጥምቀት በዓል ላይ የደረሰው አደጋ ይገኙበታል፡፡
ቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ ቸር ወሬዎች የሚሰሙበት እንዲሆን አል ዐይን ምኞቱን ይገልጻል፡፡ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት!