ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመተከል ጉብኝት ማግስት በስፍራው በርካታ ንጹሃን ተገደሉ
ኮማንድ ፖስቱ የተገደሉት ቁጥር ከመቶ ሊበልጥም ሊያንስም እንደሚችል አስታውቋል
ንጹሃኑ በዞኑ ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ላይ መገደላቸውን የዞኑ ኮማንድ ፖስት አረጋግጧል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕግ ማስከበር ያልቻሉ አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቢገልጹም እርሳቸው መተከል ዞንን በጎበኙ ማግስት በርካቶች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመከተል የሚታየውን ግድያ ለማስቆም ዕርቀ ሰላምን ጨምሮ ሌሎች የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል ቢባልም ዛሬ ማለዳ ላይ በዞኑ ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ በንጹሃን ላይ ጥቃት ተፈጽሟል መባሉ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
በኩጂ ቀበሌ በተፈጸሙት እና እጅግ ዘግናኝ ናቸው በተባሉት ጥቃቶች በርካቶች መገደላቸውን ለአል ዐይን አማርኛ የመረጃ ምንጮች አመልክተዋል፡፡
ምንጮቹ ስለ ግድያው ሁኔታ ሲገልጹ “ሰዎች ቤት ውስጥ በተኙበት በራቸው ከውጭ እየተቆለፈ ህጻናትና እናቶች ጭምር ነው የተገደሉት” ብለዋል፡፡
አል ዐይን ጉዳዩን በተመለከተ የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሽቱን እና የክልሉን የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነን ለማናገር ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ስልክ መመለስ ባለመቻላቸው ምክንያት ሀሳባቸውን ለማካተት ሳይችል ቀርቷል፡፡
በዞኑ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ቃል አቀባይ ኮሎኔል አያሌው በየነ ግን ዛሬ በቡለን ወረዳ ንጹሃን መገደላቸውን ለአል ዐይን አረጋግጠዋል፡፡
በተለያዩ አካላትና በነዋሪዎች እንደሚገለጸው የሟቾቹ ቁጥር 100 ደርሷል መባሉ እውነት እንደሆነ ላቀረበላቸው ጥያቄ ቁጥሩ ከዚህ ሊበልጥም ሊያንስም ይችላል ብለዋል፡፡
አንዳንድ ያልተረጋገጡ የመረጃ ምንጮች ግን የሟቾቹን ቁጥር እስከ 250 አድርሰውታል፡፡
በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ፣ ድባጤ፣ ቡለን፣ ዳንጉር እና ሌሎችም ወረዳዎች በተደጋጋሚ በንጹሃን ላይ ሲፈጸሙ የቆዩት ግድያዎች አሁንም ቀጥለዋል፡፡ የንጹሃኑን ጭፍጨፋ ለማስቆም የኮማንድ ፖስት ቢቋቋምም ሊቆም አልቻለም እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ፡፡
በንጹሃኑ ግድያ እና ጭፍጨፋ በመንግስት መዋቅር ላይ ያሉ አመራሮች ጭምር እንዳሉበት ይነገራል፡፡ ከአሁን ቀደም እጃቸው እንዳለበት በተጠረጠሩ 45 አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ ይሁንና አሁንም ለውጥ ለማምጣት አልተቻለም፡፡
ትናንት በስፍራው ከነዋሪው ጋር የተወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሕግ ማስከበር ባልቻሉ አመራሮች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡