“ገና ብዙ ይጠብቀናል፤ ስኬት አይቀሬ ነው”-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከህዳሴ ግድብ ጉቡኝት በኋላ
የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 76.35 በመቶ መድረሱ ከቀናት በፊት ተገልጿል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የህዳሴ ግድቡን ጎብኝተዋል
“ገና ብዙ ይጠብቀናል፤ ስኬት አይቀሬ ነው”-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከህዳሴ ግድብ ጉቡኝት በኋላ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የህዳሴ ግድቡን ሲጎበኙ የሚያሳዩ ፎቶዎችን በትዊተር ገጻቸው አጋርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተሩ “ገና ብዙ ይጠብቀናል፤ ስኬት አይቀሬ ነው” ብለዋል፡፡ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ግድቡን በመጎብኘታቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሌሎች የኢትዮጵያና የኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣናትም በጉብኝቱ ተካተዋል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ባለፈው ሐምሌ ወር ከተከናወነ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡን ሲጎበኙ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ፈወርቂ በኢትዮጵያ በጋራ እያደረጉት ባለው ሁለተኛ ቀን ጉብኝታቸው ነው የታላቁ ህዳሴ ግድብን የጎበኙት፡፡
ሁለቱ መሪዎች በቆይታቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አሁናዊ ገፅታ ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ፣ ገለፃም ተደርጎላቸዋል፡፡
መሪዎቹ ዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሰዓት በፊትም የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን ጎብኝተዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግደብ ግንባታ ሂደት 76.35 በመቶ መድረሱን የዉሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡