ቤንጃሚን ሊስት እና ዴቪድ ማክሚላን የኖቤል የኬሚስትሪ ሽልማትን አሸነፉ
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ከ3 ዓመት በፊት የኖቤል የሰላም ሎሬት ሆነው መሸለማቸው የሚታወስ ነው
‘ኦርጋኖካታሊሲስ’ የተሰኘ የምርምርና ፈጠራ ስራ በማበርከታቸው ለሽልማት መብቃታቸውን ሸላሚው ድርጅት አስታውቋል
የሮያል ስዊድን ሳይንስ አካዳሚ የ2021 የኖቤል የኬሚስትሪ ዘርፍ ሽልማትን ለቤንጃሚን ሊስት እና ለዴቪድ ማክሚላን ለመስጠት መወሰኑን አስታወቀ፡፡
አካዳሚው፤ ቤንጃሚን ሊስት እና ዴቪድ ማክሚላን ሞለኪዩሎችን ለመገንባት የሚያስችል ‘ኦርጋኖካታሊሲስ’ የተሰኘ የምርምርና ፈጠራ ስራ በማበርከታቸው ለሽልማት መብቃታቸውን አስታውቋል፡፡
3ኛውን ዓይነት የጉበት ቫይረስ በሽታ ለመለየት የተመራመሩ ሳይንቲስቶች የዘንድሮውን የህክምና ኖቤል አሸነፉ
‘ኦርጋኖካታሊሲስ’ በመድሃኒት ምርመር እና በሌሎች የኬሚስትሪ ሳይንስ ዘርፎች ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም ነው ያስታወቀው፡፡
ጃፓናዊው ሱዩኩሮ ማናቤ፣ ጀርመናዊው ክላውስ ሃስልማን እና ጣልያናዊው ጆርጂዮ ፓሪሲ የአካዳሚውን የፊዚክስ ሽልማት ሎሬትነት ማሸነፋቸው ትናንት መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ሊባኖሳዊው አርደም ፓታፖውሽያን እና አሜሪካዊው ዴቪድ ጁሊየስ ደግሞ የአካዳሚው የህክምና ዘርፍ አሸናፊ ናቸው፡፡
የአካዳሚው የስነ ጽሁፍ እና የሰላም ሽልማት አሸናፊዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ አርብ ይታወቃሉ፡፡
የምጣኔ ሃብት ሎሬት የሚሆነው ሰው ደግሞ በመጪው ሰኞ ነው የሚታወቀው፡፡
ከትናንት በስቲያ ሰኞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሃላ የፈጸሙትና በዓለ ሢመታቸውን ያካሄዱት ዐቢይ አህመድ ከ3 ዓመት በፊት የኖቤል የሰላም ሎሬት ሆነው መሸለማቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሽልማቱን ያገኙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንዲሁም ሽልማቱን በቅርቡ ያሸነፉ አፍሪካዊም ናቸው ዶ/ር ዐቢይ፡፡
ለሁለት አስርታት ያህል የዘለቀውን የኢትዮጵያ እና የኤርትራን የሻከረ ግንኙነት በማለስለስ ሰላም በማውረዳቸው ነበር ጠ/ሚ ዐቢይ የተሸለሙት፡፡
እነ ኔልሰን ማንዴላን እና ዎሌ ሶይንካን መሰል አፍሪካውያን የኖቤልን ሽልማቶች ማሸነፋቸው አይዘነጋም፡፡ ሽልማቱን ያሸነፉ አፍሪካውያን አጠቃላይ ቁጥር 25 ነው፡፡