ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ተቀበሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ዛሬ በኖርዌይ ኦስሎ በተካሄደ ደማቅ ስነ ሥርአት ተቀብለዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የኖርዌይ ንጉሳውያን ቤተሰብ አባላት፣ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ በሀገሪቱ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የተለያዩ ታዳሚያን ተገኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን ያሸነፉት ለሰላም እና አለማቀፍ ትብብር ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ነው፡፡ የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ቤሪት ሬይስ አንደርሰን እንዳሉት በተለይም የኢትዮጵያ እና ኤርትራን የቆየ የድንበር ውዝግብ ለመፍታት የወሰዱት ቆራጥ ውሳኔ ሽልማቱን ለማሸነፋቸው ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆራጥ ውሳኔ አሁን ላይ ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የድንበር ግጭት እልባት ማግኘት ከመጀመሩም ባለፈ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ተጠናክሯል፡፡
ሴቶችን ወደአመራርነት በማምጣት ረገድም ጠቅላይሚኒስትሩ የወሰዱት እርምጃ በኮሚቴው ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል፡፡ ለዚህም በሽልማቱ ስፍራ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተገኙትን የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሞፈሪያት ካሚልን፣ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን እንዲሁም ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ቤሪት ሬይስ አንደርሰን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፣ የሚዲያ ነጻነት፣ ሙስናን ለመከላከል የተሰሩ ተግባራት፣ የተቋማት ማሻሻያ እና መሰል ተግባራትም ባለፈው አንድ አመት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኗቸው ታላለቅ ተግባራት ናቸው፡፡
“ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት ሁላችንም ከጎንዎ ነን” ሲሉም አንደርሰን ለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ህዝብ በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል እና በለውጥ ጎዳና ለመምራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይነትም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ትብብርን ለማጠናከር በተለያዩ የጎረቤት ሀገራት መካከል እና እርስበርስ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት በግልና በቡድን ያከናወኗቸውን ተግባራት፣ እንዲሁም በአፍሪካ የሚፈጠሩ የብሄር እና ሌሎች ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱም የተጫወቱትን የመሪነት ሚና የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢዋ በዝርዝር አንስተው ጠቅላይ ሚኒስትሩን አመስግነዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆንዋን በመጥቀስ ‘‘ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን’’ በማለት የተናገሩት አንደርሰን ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት አለመገዛቷን እና ብዙ ታሪክ ያላት መሆኑን በመጥቀስ በዚህም የአፍሪካ ህብረት እና አንድነት ማእከል በመሆን የአህጉሪቱን ገጽታ በበጎ የምታንጸባርቅ ሀገር ናት ብለዋል፡፡ ይሄን ታሪኳንና መልካም ተሞክሮዋን አጠናክራ ልትቀጥል እንደሚገባም ነው በሽልማት ስነ-ሥርዓቱ ወቅት የተናገሩት፡፡
100ኛውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸነፉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ባደረጉት ንግግር “ሽልማቱን የኢትዮጵያና ኤርትራን ህዝብ እንዲሁም ኢሳያስ አፈወርቂን በመወከል ነው…የምቀበለው” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ጦርነት ሲጀመር ወጣት ወታደር ነበርኩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የጦርነትን አስከፊነት በጦር ግንባር ተገኝቼ አይቼዋለሁ፣ ይሄን ያላዩ አስከፊነቱ ብዙም ላይገባቸው ይችላል ብለዋል፡፡ ህጻናት፣ አዛውንቶች...ምን ያክል እንደሚሸበሩ በዋናው የባድመ ግንባር ሆኜ ተመልክቻለሁ” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
በጦርነቱ ከ100ሺ በላይ ወታደሮች እና ሲቪሎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን በመጥቀስ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውሱም ቀላል እንዳልሆነ ለታዳሚያኑ አውስተዋል፡፡
“ህዝቦቻችን አንዳቸው ለአንዳቸው ጠላት አይደሉም፣ የጋራ ጠላታችን ድህነት ነው” ካሉ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ
ዛሬ ለዓመታት የተለያዩ ቤተሰቦች መገናኘታቸውንና የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ፣ የአየር እና የቴሌኮሚኒኬሽን ግንኙነት ዳግም መጀመሩን፣ የጋራ ፐሮጄክቶችን ለመስራትም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ስለመደመርም በሰፊው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የኔ የሰላም ራዕይ በመደመር ፍልስፍና ላይ መሰረቱን ያደረገ ነው” ብለዋል፡፡
“በመደመር እሳቤ አንዳችን የሌላኛችን ጠባቂ ነን፤ ፍቅር ይቅርታና እርቅም የህይወት መርሀችን ይሆናል” ሲሉም ታዳሚያኑ በታላቅ ጭብጨባ አድናቆቱን ገልጾላቸዋል፡፡ “በመደመር እሳቤ ውስጥ እኛና እነሱ ሚባል ነገር የለም እኛ ለኛ እንጂ” ያሉት የኖቤል አሸናፊው ኢትየጵያውያን የተለያየ እምነት እና ማንነት እያላቸው ለሺዎች ዓመታት ተከባብረው የኖሩባት በዚሁ መርህ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መነሻም መደመር እንደሆነና “‘በሰላም እንድታድር ጎረቤትህ ሰላም ይደር’ እንደምንለው በተለይም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የማስተሳሰር ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡
“እንደዓለም ዜጋ ለሰላም ኢንቨስት ማድረግ አለብን፤ በተለይ ከ70 በመቶ በላይ ህዝቧ ከ 30 ዓመት በታች በሆነው አፍሪካ ወጣቱ ተስፋ እንዲኖረው ልንተጋ ይገባል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡
ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን በማስወገድ አንድነትንና ሰላምን ለማስፈን አለማቀፉ ማህበረሰብ በትብብር ሊሰራ እንደሚገባም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡