የባለፈው ዓመት የኖቤል ሽልማት ይገባቸው እንደነበር ደጋግመው የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ለሽልማቱ ታጩ
ትራምፕ ለሽልማቱ ሲታጩ ይህ የመጀመሪያው አይደለም
ፕሬዝዳንቱ ለሽልማቱ የታጩት ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም አበርክተዋል በተባለው አስተዋጽኦ ነው
ዶናልድ ትራምፕ ለኖቤል ሽልማት ታጩ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና እስራኤል የሰላም ስምምነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለኖቤል የሰላም ሽልማት ታጩ፡፡
ትራምፕ የታጩት ለስምምነቱ ስኬት ቁልፍ ሚናን ተጫውተዋል በሚል ባሞካሿቸው የኖርዌይ ምክር ቤት አባል ክሪስቲያን ታይብሪንግ ነው፡፡
በሃገራቱ መካከል ሰላምን ለማውረድ ከየትኛውም እጩ በላይ ትራምፕ ሰርቷል ሲሉም ነው ታይብሪንግ ለፎክስ ኒውስ የተናገሩት፡፡
በሽልማቱ ህግ መሰረት የምክር ቤት አባል የሆነ የትኛውም ሰው ለዓለም ሰላም መጠበቅ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል ያለውን ሰው እጩ አድርጎ ለማቅረብ ይችላል፡፡
“ታሪካዊ” በሚል የሚጠቀሰውን ስምምነት በማርሽ ቀያሪነት የጠቀሱት ታይብሪንግ ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ሊከተሉት የሚችሉት እንደሆነም ለሽልማት ተቋሙ በጻፉት የእጩ መጠቆሚያ ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡
ከካሽሚር የይገባኛል ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ያሉ ግጭቶችን ለማርገብ ጥረዋል ያሉም ሲሆን በኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላምን ለማውረድ ለፒዮንግያንግ የኒውክሌር ጉዳይ መፍትሄ ለማበጀት መታተራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ትራምፕ ለሽልማቱ ሲታጩ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር በሲንጋፖር መመካከራቸውን ተከትሎ በራሳቸው በታይብሪንግ እና በአንድ ባልደረባቸው እንዲሁም በጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በእጩነት ተጠቁመው ነበረ፡፡
ሆኖም ሻክሮ ለሁለት አስርታት የዘለቀውን የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ወደ ሰላም በመለሱት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተሸንፈዋል፡፡
ዐቢይ አህመድ ሽልማቱን ለመውሰድ የቻሉ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡
ለዘንድሮው የሰላም ሽልማት 211 ግለሰቦች እና 107 ተቋናት በድምሩ 318 እጩዎች ተጠቁመዋል፡፡